ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በአማራ ክልል፤ ባህር ዳር፣ እንጅባራ፣ አዲስቅዳም እና ቲሊሊ ከተሞች የኮሮናቫይረስ ሥርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅት ሠራተኞች እና የበጎ አድራጊ አገልግሎት ሰጭዎች በልዩ ፈቃድ እንዲንቀሳቀሱ የክልሉ ኮማንድ ፓስት ወስኗል።
በመሆኑም የመንግሥትና የግል ጤና ተቋማት ሠራተኞች፣ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች በተቋማቸው መታወቂያ፤ የጸጥታ ኃይሎች ደግሞ ያለምንም የፈቃድ ወረቀት መንቀሳቀስ እንደሚችሉ ተገልጿል።
በሌላ በኩል የውሃ መስኖና ኢነርጂ እንዲሁም የከተሞች የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮዎች፣ መብራት ኃይል፣ ቴሌኮሚዩኒኬሽን፣ መንገድ ትራንስፖርት፣ የምግብ ዋስትናና አደጋ መከላከል፣ እሳት አደጋ ፣ ጽዳትና ውበት እና የፋብሪካ ሠራተኞችን ጨምሮ ሌሎችም ልዩ የመንቀሳቀሻ ፈቃድ ይሰጣቸዋል ተብሏል።