ቅዠት ወይስ ዕውቀት? || አንተንሳይ መስፍን

ቅዠት ወይስ ዕውቀት? || አንተንሳይ መስፍን

አቶ ኃይለየሱስ አዳሙ “ቫይረሱ ይሰራጭ-በነፃነት ተንቀሳቀሱ” ሲሉን ምን ማለታቸው ነው ?

የኅብረተሰብ ጤና ከፍተኛ ባለሙያ እንደሆኑ የሚገልፁት ኃይለየሱስ አዳሙ የተባሉ ፖለቲከኛ ኮሮና ቫይረስን ለመቆጣጠር ይበጃል ብለው በፌስቡክ ገፃቸው ያቀረቡት ሀሣብ ብዙዎችን እያነጋገረ ይገኛል። ሊያነጋግርም ይገባል።

ምክንያቱም በግለሠቡ የተጠቆመው “የመፍትሔ” ሀሣብ አሁን ዓለም ከተሥማማበት ቫይረሱን የመከላከያ ና መቆጣጠሪያ ስትራቴጂ ጋር በፍፁም ተቃርኖ የቆመ ከመሆኑ በተጨማሪ ይህ ሀሣብ ጉዳዩ በቀጥታ በሚመለከተው የሙያ ዘርፍ ከተመረቁ ባለሙያ የመነጨ በመሆኑ በህብረተሰቡ ውስጥ ትልቅ ብዥታ በመፍጠር የበሽታውን መቆጣጠር ሂደት ሊያወሣሥብ የሚችል በመሆኑ ነው።

ፅሁፋቸው በአማራ ክልል አቃቤ ህግ በኩልም ሊያስከስሳቸው እንደሚችል ተጠቁሟል።

አቶ ኃይለየሱስ አሁን እንዲተገበሩ የሚሞከሩት የመከላከያ መንገዶች (እንደ በቤት መቆየት፣ እጅን አዘውትሮ መታጠብ፣ እንቅስቃሴዎችን መገደብ የመሣሠሉት) በኛ ማህበረሰብ አዋጭ እንዳልሆኑ አበክረው ባሳሰቡበት ፅሁፋቸው እርሳቸው አዋጭ ያሉትን ዘዴ በሳይንስ አሽሞንሙነው እንዲህ የሚል ድምዳሜ ላይ ያደርሱታል:-

“አትሸበሩ – ተውት ቫይረሱ ይሰራጭ፡ በነፃነት ተንቀሳቀሱ።

ከ 60 አስከ 80 በመቶ የሚሆነው ህዝብ በኮሮና ከተያዘ ህዝቡ ዘንድ herd immunity ይገነባል።
ቫይረሱ እንደ ጉንፋን መሆኑ አይቀርም …”

Herd/ community/ immunity (የመንጋ ወይም የማህበረሰብ በሽታ የመመከት አቅም) በዘርፉ ባለሙያዎች ትንታኔ –

‘በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ በቂ ብዛት ባላቸው ሰዎች (በአንድ በሽታ ተለክፈው ካገገሙ በኋላ ወይም በክትባት አማካኝነት) በሽታን የመመከት አቅም ሲፈጠር የሚገኝ የዚያን በሽታ ስርጭት መቋቋሚያ ሂደት ነው።


በክትባት የሚገኘው artificial (ሰው ሰራሽ)፤
በበሽታው የተጠቁ ሰዎች ሲያገግሙ የሚፈጠረው ደግሞ natural (የተፈጥሮ) የመንጋ በሽታ የመመከት አቅም (herd immunity ) ይሰኛል።

ይህን አቅም ገንብቶ አንድን ወረርሽኝ ለመቆጣጠር እንደተህዋሱ የተላላፊነት ብቃት የሚለያይ ቢሆንም ለአብዛኞቹ የቫይረስ በሽታዎች ከ75 እስከ 95 በመቶ የሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል በበሽታው ተጠቅቶ ማገገምን ወይም ክትባት መውሰድን ይጠይቃል ።

ወደ ኮቪድ 19 እና የአቶ ኃይለየሱስ “መፍትሔ” እንመለስ።

ቫይረሱ ክትባት ያልተገኘለት እንደመሆኑ “ከ 60 እስከ 80 በመቶ” የሚሆነው የሀገራችን ህዝብ በቫይረሱ እስኪጠቃ ድረስ በአለም ጤና ድርጅት የሚመከሩትን የበሽታው ሥርጭት መከላከያ ዘዴዎች እርግፍ አድርጎ በመተው የተፈጥሮ የመንጋ በሽታ የመመከት አቅም (natural herd immunity) መገንባትን ነው አቶ ኃየለየሱስ በልበሙሉነት የሚመክሩን።

ይኽንን ቫይረሱ ከያዛቸው ሰዎች ምን ያህሉን ለጠና ህመም ይዳርጋል ምን ያህሉትንስ ለሞት ያበቃል የሚሉትን በጥናት የተደረሰባቸው ምጣኔዎች በእኛ ህዝብ ቁጥር ስናሰላ ለመከወን ቀርቶ ለማሠብ የሚያስደነግጡ ውጤቶች እናገኛለን።

ከርሳቸው መላምት ዝቅተኛውን 60 በመቶ ብንይዝ ና የሀገራችንን ህዝብ ብዛት 100 ሚሊዮን ብናደርገው፤ 60 ሚሊዮን ሰው በቫይረሱ መያዝ ይኖርበታል።

አሁን ባለው ሁኔታ ብዙ ሰዎችን ለመመርመር ባለመቻሉ ሳቢያ የቫይረሱ የገዳይነት ምጣኔ (case fatality rate) ብዙዎችን ያስማማ ባይሆንም የተሻለ ተብሎ የተያዘው ግምት ከ 0.5 አስከ 1 በመቶ የሚለው ነው።

የገዳይነት ምጣኔ በቫይረሱ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር በቫይረሱ መያዛቸው ለተረጋገጠው ሰዎች ቁጥር ተካፍሎ በመቶ ሲባዛ የሚገኝ ስሌት ነው።

በዚህ ቀመር በትንሹ ምጣኔ 0.5 በመቶ ስናሠላ ከ60 ሚሊየን በቫይረሱ የተያዙ ውስጥ 300,000 (ሶስት መቶ ሺህ) ሰዎች ይሞታሉ ማለት ነው። ይህ እንኳን የዕቅድ አካል ሊሆን ለማሠብ የሚዘገንን አሃዝ ነው።

የአቶ ኃይለየሱስ “መፍትሔ” ፍፁም ሊታሠብ የማይደፈር ለመሆኑ ይኼ በቂ ማሣያ ቢሆንም ለመጨመር ያህል የታማሚነት ምጣኔንም እንመልከት።

በኮቪድ 19 ከተያዙ ሰዎች የሆስፒታል ህክምና የሚያስፈልጋቸው በጠና የሚታመሙ ሰዎች ምጣኔ 10 በመቶ እንደሚሆኑ ጥናቶች ይገምታሉ። በዚህ ስሌት ደግሞ 6 ሚሊየን ፅኑ ህሙማን ይኖሩናል ማለት ነው ።

በዚች ድሀ ሀገር አቅም በነባር በሽታዎችና አደጋዎች የሚታመሙትን ሳንደምር ይኸን ያህል ቁጥር ያላቸው ህሙማንን እንዴት ማስተናገድ እንችላለን ? የሀገሪቱ ሁለንተናዊ የጤና አጠባበቅ አቅምስ ይፈቅዳል ወይ?

እንኳን እኛ አቅም አላቸው የሚባሉ ሀገሮች ከ 20,000 (ሀያ ሺህ) የማይበልጡ ከፍተኛ ክትትል የሚያሻቸው ፅኑ ህሙማን መንከባከብ ተስኗቸው እየተንገዳገዱ የኛ ኤክስፐርት እንዴት ቀልሎ እንደታያቸው የሚያውቁት እርሳቸውና ያሳሰባቸው መንፈስ ብቻ ናቸው።

እነዚህ ሁኔታዎች የሚፈጥሩት ለግምት የሚያዳግቱ ሁሉን ዳሰስ ማህበራዊ ቀውሶችስ አልታዩአቸው ሆኖ ነው ወይስ ለኔ ያልታየኝ እና በፅሁፋቸው ያልጠቀሱአቸው ሌላ ታሳቢ ጉዳዮች ኖረው ይሆን?
ግለሰቡ የብልፅግና ፓርቲ የሚያደርጋቸው ስብሰባዎች የበሽታውን ስርጭት ለማስፋፋት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለው በተቹ በሶስተኛው ቀን በተቃራኒው መሠብሰብን የሚያበረታታ ሃሣብ ይዘው መምጣታቸው የቫይረሱን ስርጭት ለፖለቲካ ግብ የሚጠቀሙበት አንዳች እንግዳ ስትራቴጂ ተከስቶላቸው ይሆን?

LEAVE A REPLY