ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የኮቪድ 19 ስርጭትን ለመቆጣጠርና ብሎም ለመግታት ያስችለኛል ያለውን የቤት ለቤት ምርመራ ነገ የሚጀምር መሆኑን ቢገልጽም የከተማዋ ነዋሪዎች ግን በምርመራው አስተማማኝነት ላይ ከወዲሁ ስጋታቸውን እየገለፁ ነው።
የኢትዮጵያ ነገ የአዲስ አበባ ሪፖርተራችን ያነጋገራቸው ነዋሪዎች መንግሥት የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር የሚያደርገው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው ነገ የሚጀምረው የቤት ለቤት ምርመራ በምን ሰዐት የትኛው ወረዳ ላይ እንደሚደረግ ጥርት ያለ ፕሮግራም አለመነደፉና አሠራሩ ለሕዝብ ግልፅ አለመሆኑ በውጤታማነቱ ረገድ ጥርጣሬ እንዲገባቸው ማድረጉን ተናግረዋል::
“እስከ ዛሬ እሁድ ከሰዐት በኋላ ድረስ ኅብረተሰቡ ምንም ዓይነት ዝርዝር መረጃ የለውም:: የሕክምና ባለሙያዎቹ በየትኛው ቀን የት አካባቢ የቤት ለቤት ምርመራውን እንደሚያደርጉ አልገለፁም:: የአዲስ አበባ አብዛኛው ነዋሪ በግል ድርጅቶችና በግል ሥራ እንዲሁም በዕለት ተዕለት ገቢ የሚንቀሳቀስ እንደመሆኑ መጠን ወደ መደበኛ ሥራው በሄደበት ወቅት የሚካሄድ የቤት ለቤት ምርመራ የአንድን ቤተሰብ ጤንነትና ከቫይረሱ ነፃ የመሆን ዕድል አያረጋግጥም” ያሉት አስተያየት ሰጪዎች በተጠቀሱትና በሌሎች ምክንያቶች በምርመራው ያልተካተቱ ሠዎችስ ቀጣይ ዕጣ ፈንታቸው ምን ሊሆን ይችላል? ሲሉ በአሠራር ረገድ ሊኖር የሚችለውን ክፍተት በተመለከተ ጥያቄ ያቀርባሉ።
በሌላ በኩል ዓለም ላይ የበለፀጉ የሚባሉ ሀገራት ለዜጎቻቸው የኮቪድ 19 ቫይረስ የቤት ለቤት ምርመራ ማድረግ ቢፈልጉም በቂ የሆነ የመመርመሪያ መሣሪያ እጥረት ዋነኛ ችግራቸው መሆኑን እየገለፁ ባለበት ወቅት ኢትዮጵያ ምን ያህል ዘመናዊ የመመርመሪያ መሣሪያ ቢኖራት፣ ጥራትና ብቃቱስ ምን ያህል አስተማማኝ ቢሆን ነው ምርመራውን ቤት ለቤት ለማድረግ የተነሳችው ሲሉ እነዚሁ ነዋሪዎች ይጠይቃሉ።
እነዚህን መሰል ወሳኝ ጥያቄዎችን በተመለከተ የተሰጠ በቂ ማብራሪያ ባይኖርም የኢ/ር ታከለ ኡማ አስተዳደር ግን ነገ በአዲስ አበባ የቤት ለቤት ምርመራ እጀምራለሁ ሲል ዳግም ማረጋገጫ ሰጥቷል።