የፌደራል ፖሊስና የአ/አ ፖሊስ አባላት የሚሰበሰቡ ወጣቶችን መበተን ጀመሩ

የፌደራል ፖሊስና የአ/አ ፖሊስ አባላት የሚሰበሰቡ ወጣቶችን መበተን ጀመሩ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የሚኒስትሮች ም/ቤት በአስቸኳይ ስብሰባው ያወጣውንና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያፀደቀውን አዲስ አዋጅ ተከትሎ ህግ አስፈጻሚ አካላት የተለያዮ እርምጃዎችን መውሰድ ጀመሩ።

አዋጁ ከፀደቀ በኋላም ቢሆን ዝርዝር ይዘቱ በግልፅ ያልተብራራ መሆኑን ተከትሎ ኅብረተሰቡ በግራ መጋባት ውስጥ ቢቆይም ትናንት ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ሠፊ ትንታኔ ሰጥቶበታል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በዋነኝነት የተቀመጠው የአካላዊ ንክኪ ርቀትን መጠበቅ እንደመሆኑ መጠን በየትኛውም ቦታ ላይ ከአራት ሠው በላይ እንዳይሰበሰብ የማድረጉ ሥራ ከዛሬ ማለዳ ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ተግባራዊ ሆኗል::

በዚህም መሠረት አዋጁን ተከታትለው በትክክል እንዲተገብሩ ሥልጣን የተሰጣቸው የፌደራል ፖሊስና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት በመዲናዋ የተለያዮ ቦታዎች ከአራት በላይ ሆነው ተሰብስበው የነበሩ ወጣቶችን በየመንደሩ በመግባት ሲበትኑ ታይተዋል:: የፀጥታ ኃይሎቹ በካፌና ሬስቶራንት በረንዳዎች ላይ ከሆሳዕና ክብረ በዓል መልስ ተሰባስበው ቁርስ ሲመገቡ የነበሩ ወጣቶችንም በተመሳሳይ ሁኔታ ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲቀመጡና የሠዎች ክምችትን ሲበትኑ ታይቷል።

የፖሊስ አባላቱ ሕዝቡ ለአዋጁ ተፈጻሚነት ምንም ትኩረት ሳይሰጥ እንዲሁ እንደተለመደው በዘፈቀደ መንቀሳቀሱ ፣ ብሎም  ቫይረሱን ለመቆጣጠር ለሚደረገው ርብርብና ጥረት ደንታ ቢስ መሆኑ በእጅጉ ቢያበሳጫቸውም የተሰበሰቡ ሰዎች ላይ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ በመምከርና በቂ ማብራሪያ መስጠታቸው በእጅጉ የሚያስመሰግን ሆኖ ታይቷል።

አሁን ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ያለው የኅብረተሰቡ እንቅስቃሴ በጣም አሳሳቢ መሆኑን ለሪፖርተራችን የገለፁት አንዳንድ ነዋሪዎች በሚታየውና እየደረሰ ባለው አደጋ ያልተደናገጠው ሕዝብን በቀጣይ በደንብ ግንዛቤ ሊያስጨብጡ የሚችሉ እርምጃዎችን መንግሥት መውሰድ እንዳለበት አሳስበዋል።

LEAVE A REPLY