ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ተከትሎ ከመደበኛ የተሳፋሪ ጭነት በግማሽ ያህል ቀንሰው ስድስት ሰው ብቻ እንዲጭኑ የተደረጉት የአዲስ አበባ ሚኒባሶች የተሳፋሪ ንክኪን ተከትሎ ለኮሮና ቫይረስ ስርጭት መስፋፋት ተጋላጭ እንደሚያደርግ ነዋሪዎች ገለፁ።
ሚኒ ባስ ታክሲዎቹ በወጣው መመሪያ መሠረት የተሳፋሪን ቁጥር ስድስት ሰው ብቻ ማድረጋቸው መልካም መሆኑን ያልሸሸጉት አስተያየት ሰጪዎች አብዛኛው የመዲናዋ ታክሲዎች መመሪያውን ተከትሎ ያለ ረዳት በሹፌር ብቻ መስራታቸው ተጓዦች በሚገቡና በሚወርዱበት ወቅት የሚኒባሱን በር እራሳቸው ለመክፈትና ለመዝጋት እንደሚገደዱ አስታውሰው ይህ ዓይነቱ አሠራር ቀኑን ሙሉ የሚተገበር መሆኑ የቫይረሱን ስርጭት በማሣደግ ረገድ ድርሻው ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ቅድመ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
በአዲስ አበባ የሚገኘው የኢትዮጵያ ነገ ዘጋቢ ያነጋገራቸው በተለያዮ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ሚኒ ባሶቹ ረዳት (ወያላ) አልባ በመሆናቸው ተሳፋሪ በገባና በወረደ ቁጥር በሚኖረው የተለያዮ ተሳፋሪ ሰዎች የእጅ ንክኪ ምክንያት ስጋት የሆነብን የኮሮና ቫይረስ በፍጥነት ሊስፋፋና ሊያድግ እንደሚያስችል ገልጸዋል።
በመሆኑም መመሪያውን ያወጣው መንገድ ትራንስፖርትም ሆነ ህግ አስፈጻሚው ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ያለ ረዳት በሹፌር ብቻ በሚንቀሳቀሱ የመዲናችን ሚኒባስ ታክሲዎች ላይ በትክክል የሚተገበር ቅጣትና መመሪያ በፍጥነት ሊያወጡ እንደሚገባ ለኢትዮጵያ ነገ ተናግረዋል።