ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኮቪድ 19 ቫይረስ ስርጭትን ተከትሎ ትምህርት ቤቶች ቢዘጉም ልጆቻቸው ላልተማሩበት እንዲከፍሉ የተጠየቁ ወላጆች መኖራቸውን ተከትሎ መንግሥት በግል ት/ቤቶች ላይ አዲስ ውሳኔ ሊያሳልፍ መሆኑ ታወቀ።
ወረርሽኙን ተከትሎ ከመጋቢት 7ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ መንግሥት ትምህርት ቤቶችን ለ15 ቀን ቢዘጋም ውሳኔው ከፍ ብሎ እስካሁን ድረስ በመላ ኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ዝግ እንደሆኑ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ የግል ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን ላላስተማሩበት ወላጆች ወርሀዊ ክፍያ እንዲከፍሉ መደረጉ ወላጆችን ክፉኛ አሳዝኗል።
ይህንን የወላጆች ቅሬታ ተንተርሶ በጉዳዮ ላይ መንግሥት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑ ተነግሯል። የንግድ ውድድርና ሸማችች ጥበቃ ባለ ሥልጣን አቤቱታ ምርመራ ዳይሬክተር አቶ ጌትነት አሸናፊ በመንግሥት በኩል እስከ መቼ ድረስ ትምህርት እንደሚቋረጥ አለመታወቁ ውሳኔ ለመስጠት አስቸግሯል ይላሉ።
ይህ አሠራር ከጠራና በትክክል፣ በእርግጠኝነት ውሳኔውን መለየት ከተቻለ በኋላ ወላጆች ለተጠቀሱት ጊዜያት የልጆቻቸውን ክፍያ መክፈል እንደማይገባቸው የጠቆሙት ሓላፊ በቀጣይም እንዲህ ዓይነት ችግር እንዳይፈጠር በመንግሥት በኩል ጠንከር ያለ አዲስ ውሳኔ ለማሳለፍ እየተዘጋጀ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የትምህርት ቤት ክፍያን ወላጆች እንዳይከፍሉ ከተደረገ ት/ቤቶች የመክፈል አቅም ስለማይኖራቸው የአስተማሪዎች ደምዎዝ ሊቋረጥ ይችላል የሚል ስጋት በበርካታ የግል ትምህርት ቤት በሚሠሩ መምህራን ዘንድ እየታየ ነው። ይህ የሚሆን ከሆነ ደግሞ ከፍተኛ የህነ ማኅበራዊ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል ባለሙያውች ይናገራሉ።