የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን || ፕሮፍ. መስፍን ወልደ ማርያም

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን || ፕሮፍ. መስፍን ወልደ ማርያም

ሚያዝያ 2012

ችግር ሁልጊዜ አንዳንድ መልካም ነገሮችን ይዞ ይመጣል፤ የዘመኑ ወረርሺኝም በእኔ አስተያየት ሁለት ጥሩ ነገሮችን አስከትሏል፤ አንዱና ዋናው ከጃንሆይ በኋላ ተሸሮ የነበረው እግዚአብሔርን መልሶ በቦታው ማስቀመጡና በየመገኛዎች የእግዚአብሔርን ስም ማንሣት ተለመደ፤ ይህ ትልቅ ንቃት ነው።፤ እግዚአብሔር ሁሌም በመንበሩ ላይ ነው፤ አይነቃነቅም፤ ሁለተኛው የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ተረስታ ወደ ጓዳ ተደብቃ ነበር፤ ዛሬ ጉልበትዋ በሙሉ ባይሆንም ታየ፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዝናዋ አልተነገረም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያለበትን ውለታ ገና በትክክልና በዝርዝር የሚናድረው አላገኘም፤ እንደተዳፈነ ነው፤ ቤተ ክርስቲያኒቱን ተደግፈው የሚወጡ ሁሉ በሥልጣኑ ጣዕምና ሙቀት እዚያው ቀልጠው ይቀራሉ፤ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ለአሥር እውነተኛ ተማሪዎች የሊቅነት ማዕርግ የሚያሰጣቸው ነው፤ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የትምህርት ሚኒስቴር ነበረች፤ የበጎ አድራጎት ሚኒስቴር ነበረች፤ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ነበረች፤ የባህልና የቅርስ ጥበቃ ሚኒስቴር ነበረች…

በዛሬው ጊዜ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የተማሩ ሰዎች አላጣችም፤ በጥቁርና በነጭ ልብስ የተሸሞነሞኑ ዓለማውያን ናቸው፤ እንደአቡነ ተክለ ሃይማኖት ያለው እንኳን ደፍሮ ጉልበተኞችን መጋፈጥ አልቻሉም፡፡

LEAVE A REPLY