የሰው ልጅ ሳንባ በአማካይ 500 ሚለየን የሚሆኑ ትናንሽ አየር መሳቢያ ፊኛ (alveoli) አሉት። የነዚህ ፊኛዎች ጤና የምንስበውን የአየር ብሎም የምናገኘውን ኦክስጂን መጠን (gas exchange) ይወስነዋል። አየር ወደ ውስጥ ስንስብ እኚህ ፊኛዎች እስከሚለጠጡ ይሞላሉ፡፡ ከነዚሀ ፊኛዎች ጀርባ የሚገኝ ቀጭን የደም ስር (perialveolar capillary) የአየር ፊኛዎቹ ሲሞሉ (ሲለጠጡ) በግድግዳቸው ላይ አምልጦ የሚተንለትን (diffusion) አክሲጅን ተቀብሎ ወደ ሰውነት ይዞ ይገባል እግረ መንገዱንም የያዘውን ቆሻሻ ጋዝ (CO2) ወደ አየር ፊኛ ያተናል፡፡ በዚህ ሒደት አክሲጂን አገኘን ህይወትም ቀጠለች ማለት ነው፡፡
በሰው ልጅ ተፈጥሮ በአየር ፊኛ (alveoli) እና ኦክሲጂን ተቀብሎ በሚወስደው የደም ስር (Capillary) መካከል ያለው ግድግዳ እጅግ እጅግ ሲበዛ ቀጭን ነው፡፡ ኦክስጂን ወደ ሰውነት መግባትም ሆነ ጒጂ የየሆነ ጋዝም መውጣት (gas exchange) ሊካሔድ የሚችለው ቅጥነቱ እንደተጠበቀ ከኖረ ብቻ ነው።
የኮሮና በሽታ ሲከፋ (Sever form) ይህ ወሳኝ አካባቢ በሰውነት መከላከያ ይደበደባል። በመሆኑም የአየር ፊኛውም ሆነ የደም ስሩ ግድግዳ ይቆስላል፡፡ የአየር ፊኛው ጀርባ ያለው የደም ስር ስለሚቀደድ በደምስሩ ውስጥ የነበረ ፈሳሽ እና ፕሮቲን (plasma protein) ደምስሩን ለቆ ይወጣል… አየር ፊኛው በፈሳሽ ይጥለቀለቃል (proteinaceous excudates in alveolar space)። አካባቢው በፈሳሽ፣ በሞቱ ወታደሮች እና ቆሻሻ ይሞላል፡፡ የፈነዳውን የአየር ፊኛም ለመድፈን በሚደረገው የጥገና ስራ በጠባሳ ይሞላል(pneumocyte hyperplasia)፡፡ ጠባሳው ደግሞ ወፍራም ስለሚሆን ቢጠገንም ግድግዳዉ ኦክስጅን አያሳለፍም ወይም በቀላል ቋንቋ ስስ የነበረው ፊኛ የዘይት ጀሪካን ሆነ ማለት ነው። አይለጠጥም… አየር ብንስብበት እንኳ አክሲጂን አያሳልፍም… ዋጋ የለውም፡፡ በዚህም አየር ማስተላለፍ ኖሮበት የማያስተላልፍ ሰነፍ ክፍል በሳንባችን ይጨምራል (rise in physiologic dead space)፡፡ የዚሀ አይነት ሳንባ ክፍል እንደሞተ ይቆጠራል። ሰውነት እና የአየር ፊኛው እንደተለያዩ ይቀራሉ!
ሰውየው ከኮሮና ከዳነ የተረፈ ቢመስልም ካሉት 500 ሚሊየን አየር መሳቢያ ፊኛ (alveoli) ውስጥ ምናልባት 300 ሚለየን ገብሮ ሞተውበት ሊሆን ይችላል …ቀሪ ህይወቱን በ200 ሚለየን ፊኛ ይጋፈጣል እንደማለት ነው። በሌላ ቋንቋ ስድስት ሲለንደር መኪናን ባለ ሁለት ቢደረግ ችግሩ ምን ይሆናል ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ… V8 ወደ ላዳነት ቢቀየር ለውጡ የሚታወቀው ዳገት ላይ ሊሆን ይችላል… መዳኑ ያለ ኪሳራ አይደለም፡፡ የእድሜ ልክ ችግር ጥሎ የሚሔድ በሽታ ነው።
ሌላ ጊዜ ኮሮና ኩላሊትን እንዴት እንዳሚጐዳ እነግራችራዋለሁ።
የዚህ ፅሁፍ የተፃፈበት አላማ የባህሪ ለውጥን ለማፋጠን ነው… According to cognitive behavior change model… አንዳንድ ሰዎች የሚጠነቀቁት ነገሩን በትክክል ካወቁት/ከተረዱት ብቻ ነው… በተፈጥሮ በቀላሉ አያምኑምና፡፡ እናም በዚህ መረጃ ተመርቶ ራሱን ለመጠበቅ የሚወስን አይጠፋም ብየ ተስፋ አደርጋሁ፡፡
ከኮኖና ራስዎን ቤተሰብዎን አገርዎን ይጠብቁ!
|| ከዶ/ር KH Abate ፌስ ቡክ ገጻቸው የተወሰደ ||