ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ቁጥሩ እያሻቀበ የሚገኘው የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ ተጨማሪ ሠባት ሰዎች ዛሬ ቫይረሱ እንደ ተገኘባቸው የጤና ሚኒስቴር ገለፀ።
ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ለ401 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎ ሠባት ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታውቀዋል። በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 92 ደርሷል።
ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰባቱም ግለሰቦች ኢትዮጵያውያን ናቸው:: ከእነዚህም ውስጥ 6ቱ የጉዞ ታሪክ ያላቸው እና በለይቶ ማቆያ ውስጥ የሚገኙ ሲሆኑ ፣ አንዷ ደግሞ የጉዞ ታሪክ የሌላትና ንክኪ እንደነበራት ለማወቅ በመጣራት ላይ ይገኛል ተብሏል።
የ21 ዓመት እና የ51 ዓመት እድሜ ያላቻው ኢትዮጵያውን ከአሜሪካ የመጡ ሲሆን ፣ የ76 ዓመት እና የ34 ዓመት እድሜ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ደግሞ ከስዊድን የመጡ እና ሁሉም በለይቶ ማቆያ ውስጥ የሚገኙ መሆናቸው ተረጋግጧል።
የ32 ዓመት ኢትዮጵያዊ የጀርመንና የቤልጂየም የጉዞ ታሪክ ያለው፣ እንዲሁም የ39 ዓመት ኢትዮጵያዊ ደግሞ ከጃፓን የመጣ ሁለቱም በለይቶ ማቆያ ውስጥ ያሉ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች መሆናቸውን የጠቆመው መግለጫ አንዲት የ14 ዓመት ሴት ኢትዮጵያዊት ደግሞ የጉዞ ታሪክ የሌላት ቢሆንም በቫይረሱ መያዟን በምርመራ ማረጋገጥ መቻሉን ያሳያል።