“ቪክቶርያ ጋርደን” || ሙሼ ሰሙ

“ቪክቶርያ ጋርደን” || ሙሼ ሰሙ

“ቪክቶርያ ጋርደን” ወይም “ዎር ጋርደን” በ1917 በተለይ ጦርነቱ የፈጠረውን የአቅርቦት ክፍተት ለማገዝ በካናዳ በአሜሪካና በእንግሊዝ የተቀጣጠለ ጓሮን የማልማት ሕዝባዊ ንቅናቄ ነበር። ንቅናቄው የተጀመረው አምራች የሆነው ሃይልና ለምርት የሚሆነው መሬት በጦርነቱ ምክንያት በከፍተኛ ደረጃ ስለተጎዱና ምርት ተመናምኖ ስለነበር ነው።

ችግሩን ለመቋቋም አቅርቦትን ራሽን የማድረግ አስገዳጅ ሁኔታ ስለተፈጠረ፣ ማህበረሰቡ ራሽኑን ከማማረር ይልቅ በራስ ተነሳሽነት በግልና በጋራ ተጣምሮ በንቅናቄው አማካኝነት ጓሮን በማልማት የራሱን ድርሻ እንዲወጣ አግዟል። ይህው ተሞክሮ፣ በ2ኛው የዓለም ጦርነት ጊዜም ጎልብቶ፣ በርካታ መራሄ መንግስታትና ቤተ መንግስቶች በጓሮ አትክልት ልማቱ ተሳትፈው ነበር።

ችግሩን ለመቅረፍ የከተማ ነዋሪዎች በከተማ ውስጥ ግብርና ላይ መሰማራት በመቻላቸው ምክንያት፣ የራሳቸውን አቅርቦት ሸፍነው፣ ለገበያ የሚሆን ምርት እስማቅረብም ደርሰው ነበር። በ1918 በካናዳ ብቻ ከ5.4 ሚሊየን በላይ የከተማ ውስጥ የጎሮ አትክልት ቦታዎች መስፋፋት ችለው ነበር። በወቅቱ አምራቾቹ የራሳቸውን ፍጆታ ትተን ከ1.59 ሚሊየን ኪሎ በላይ የፍራፍሬና የአትክልት ምርት ለገበያ ማቅረብ አቅርበዋል። ጦር ሜዳ ያልዘመቱ ዜጎች ( Home Front) በጓሮ አትክልቱ ልማት ምክንያት፣ ለጦርነቱ ከፍተኛ አስተዋጾ ማድረጋቸው፣ በሕዝብ ዘንድ ትልቅ የአርበኝነት መንፈስም ፈጥሮ ነበር።

ዛሬ አጀንዳው ቢለይም ከጦርነት የማይተናነስ አደጋ ከፊታችን ተጋርጧል። መንግስት ተገዶ ወደ አቅርቦት ራሽን ሊገባ ይችላል ። በቀጣይ ችግሩን በጋራ ለመወጣትና ጫናውን ጋብ ለማድረግ እንዲቻል፣ ሰፋፊም ሆነ ትንሽ ቦታ ያላቸውን የከተማ ነዋሪዎች ቦታቸውን አብቃቅተው ጓሯቸውን በማልማት፣ ራሳቸውን እንዲችሉ፣ ገበያውን እንዲደግፉና ኢኮኖሚውን እንዲደጉሙ ማድረግ ይገባል።

ተነሳሽነቱን በተቀናጀ መልክ በመፍጠር፣ አስፈላጊውን ሙያዊ ድጋፍ በማድረግና እውቀትን በማጋራት መንግስትና መገናኛ ብዙሃን የድርሻችውን ቢወጡ፤ በድምር ውጤቱ ገበያውን በአቅርቦት በመደገፍ፣ ለኢኮኖሚውም መልካም እድል በመፍጠር ሰፊ መዳረሻ መሆን ይቻላል።

በዚህ መንገድ ከተባበርን፣ በአንድ በኩል በጋራ ኢኮኖሚያችንን በመደገፍ፣ በሌላ ጎን እራሳችንን በስራ በመጥመድ፣ አልፎ ተርፎም የስራ እድልና ገቢ በመፍጠር የዜግነትና የሞራል ኋላፊነታችንን መወጣት እንችላለን።

LEAVE A REPLY