ቀነኒሳና ኪፕቾንጌ ቀጠሮ የያዙበት የበርሊን ማራቶን ላልተወሰነ ጊዜ ተራዘመ

ቀነኒሳና ኪፕቾንጌ ቀጠሮ የያዙበት የበርሊን ማራቶን ላልተወሰነ ጊዜ ተራዘመ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ከስድስቱ የዓለማችን ታላላቅ የስፖርት ውድድሮች መካከል ቀዳሚዎቹ የበርሊንና የለንደን ማራቶን በተያዘላቸው ጊዜ እንደማይካሄዱ ተገለፀ።

የበርሊን ማራቶን በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ሴፕቴምበር 27 ቀን 2020 ለማካሄድ የታቀደ ቢሆንም ጀርመን የእንቅስቃሴ ገደቧን እስከ ጥቅምት ወር መጨረሻ ድረስ በማራዘሟ የተነሳ ውድድሩ አይከናወንም ተብሏል።

የውድድሩ አዘጋጆች ስፖርታዊ ውድድሩ በታቀደለት ጊዜ “አይካሄድም” ከማለት ውጭ ለሌላ ጊዜ ስለመተላለፉና መቼ እንደሚካሄድ በግልፅ ከማስታወቅ ተቆጥቧል።

ትልቁ የበርሊኑ ውድድር ለማካሄድ ፕሮግራም ተነድፎ የነበረው ከለንደኑ ማራቶን በፊት ፣ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ሲሆን ዘግየት ብሎ ግን የለንደኑ ማራቶን ወደ ኦክቶበር 4 መገፋቱ ይታወሳል። የለንደኑ ማራቶን በመጀመሪያ እቅዱ መሰረት ፣ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ለመካሄድ እቅድ ተይዞ ነበር :: ሆኖም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ተደርጓል።

የበርሊን ማራቶን ምናልባትም በሕዳር ወር አጋማሽ ሊካሄድይችላል ተብሎ ቢገመትም  ፤ ያ ወቅት ደግሞ የኒውዮርኩ ማራቶን እንደሚካሄድ መገለፁ ለአትሌቶችም ሆነ ለአዘጋጆች ፈታኝ ይሆናል እየተባለ ነው።

የበርሊን ማራቶን ፈጣን ውድድር ሲሆን ባለፉት አመታት በወንዶች ማራቶን ውድድር ሰባት ጊዜ ክብረ ወሰን ተሻሽሎበታል። እ.ኤ .አ በ2018 ኬንያዊው ኤሉድ ኪፕቾጌ ሁለት ሰዐት ከአንድ ደቂቃ ከ39 ሰከንድ በመግባት ክብረወሰኑን በእጁ ያስገባ ሲሆን ፤ ባለፈው ዓመት ቀነኒሳ በቀለ ሁለተኛው ፈጣን ሰዐት ሆኖ የተመዘገበውን 2:01:41 በመግባት አሸንፏል::

እነዚህ ሁለት ታላላቅ አትሌቶች የበላይነታቸውን ለማስጠበቅ በዚህ ዓመት ከኪፕቾጌ ጋር በለንደን ማራቶን ለመፎካከር ቀጠሮ ይዘው እንደነበር ዓለም ዐቀፍ ሚዲያዎች በመዘገብ ላይ ናቸው።

LEAVE A REPLY