ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሁሉም የኢንዱስትሪ ፓርኮች የኮሮና ቫይረስ ምልክቶችን ለመለየት የሚያስችል ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ከትናንት ጀምሮ መጠቀም ጀምረዋል ተባለ።
ቴክኖሎጂው በአንድ ጊዜ በብዙ ሠራተኞች ላይ የቫይረሱ ምልክቶች ስለመታየት አለመታየታቸው ለማወቅ ያስችላል መባሉንም ሰምተናል።
ከዚህ በፊት የእያንዳንዱ ሠራተኛ የሙቀት መጠን በግንባሩ አቅጣጫ በሚያዝ ትንሽ መሣሪያ እየተለካ ወይም እየተመረመረ ሥራ ላይ ይሠማራ ባ እንደነበር የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽ ገልጿል።
የነበረው አሠራር ረጅም ጊዜ የሚፈጅ እንደ ነበርም በኮርፖሬሽኑ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን አገልገሎት ሓላፊ አቶ ደርቤ ደበሌ ጠቁመው፤ ከትናንት ጀምሮ ግን ሁሉም የኢንዱስትሪ ፓርኮች በአንድ ጊዜ ለብዙ ሠራተኞች አገልግሎት መስጠት ያስችላል የተባለውን ዘመናዊ መሣሪያ መገልገል ጀምረዋል ብለዋል።
የሃዋሳ እና አዳማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ዘመናዊውን ቴክኖሎጂ ቀደም ብለው መጠቀም የጀመሩ ፓርኮችናቸው። በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የተወሰኑ ሠራተኞቻቸው እረፍት እንዲወጡ ያደረጉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች አሁን ወደ ሥራቸው እንዲመለሡ ወስነዋል:: ከሠራተኞቻቸው የተወሠኑትን በዕረፍት ላይ ካቆዩት መካከል የመቀሌ እና ሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ዋነኞቹ ናቸው።
የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሡት ቫይረሱበፈጠረው ተፅዕኖ ምክንያት ለምርቶቻቸው ከተለያዩ ሀገራት የሚቀርበው ጥያቄ በመቀዛቀዙ ነው ተብሏል። አሁን ፍላጎቱ እንደገና እያንሠራራ በመምጣቱ እነሱም ሠራተኞቻቸውን ከዕረፍት መመለስ ጀምረዋል።
ሥራ በጀመሩ ሰባት የኢንዱስትሪ ፖርኮች ከ70 ሺህ በላይ ሠራተኞች አሉ። ቀሪዎቹ አምስት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ ሲገቡ ደግሞ ይህ ቁጥር በእጅጉ እንደሚጨምር ነው የተነገረው።