ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ሲባል በሀገር ውስጥና በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በተጣሉ የእንቅስቃሴ ገደቦች የተነሳ በአዲስ አበባ የሚገኙ ሆቴሎች በከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ ወድቀዋል ተባለ::
በወጣው መረጃ መሠረት በዋና መዲናዋ የሚገኙ ሆቴሎች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በየወሩ ከ1.1 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ እያጡ ነው ተብሏል፡፡
ጉዳዮን አስመልክቶ የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማኅበር ሰሞኑን ይፋ ባደረገው የጥናት ውጤት መሰረት፤ በአዲስ አበባ ከሚገኙና የማህበሩ አባል ከሆኑ 130 ሆቴሎች ውስጥ ፣ 66 በመቶ ያህሉ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ሊዘጉ ይችላሉ ተብሎ ተገምቷል።
የሆቴሎቹ መኝታ ክፍሎች ፆማቸውን ማደር ከጀመሩ ሰንበትበት ማለታቸውን የዳሰሳ ጥናቱ አረጋግጧል፡፡ 130 የሚደርሱት ሆቴሎች በአጠቃላይ 8,997 መኝታ ክፍሎች እንዳላቸው ያመላከተው ጥናት፤ በአሁኑ ወቅት ከእነዚህ አልጋዎች 2 በመቶ ያህሉ ብቻ ተይዘው እንደሚያድሩ አስታውቋል፡፡
በማኅበሩ ስር ከተሰባሰቡት ሆቴሎች ውስጥ 38 በመቶ ያህሉ ባለሦስት ኮከብ፤ 19 በመቶዎቹ ባለ 4 ኮከብ መሆናቸውን የጠቆመው ጥናት፤ ከእነዚህ ውስጥ 88 በመቶዎቹ በኮሮና ሳቢያ ሙሉ ለሙሉ አሊያም በከፊል ሊዘጉ ይችላሉ፤ በዚህም የሠራተኞቻቸው እጣ ፈንታ ለአደጋ ይጋለጣል ሲል ስጋቱን ገሀድ አውጥቷል፡፡
እነዚህ ሆቴሎች በጠቅላላ በሥራቸው ለሚያስተዳድሯቸው ከ15 ሺህ በላይ ሠራተኞች ደሞዝ መክፈል እየተቸገሩ መሆኑንም መረጃው ያሳያል፡፡