ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የ”ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ” ፓርቲ መስራችና ሊቀ መንበር እስክንድር ነጋ ዛሬ በፖሊሶች ከመንገድ ላይ ተይዞ ከታሰረ በኋላ መፍታት በርካቶችን አስቆጥቷል።
ሰሞኑን በመላ አዲስ አበባ ኅብረተሰቡ በኮሮና ቫይረስ ስጋት ውስጥ መውደቁን ተከትሎ ከፍተኛ ማኅበራዊ ድጋፎችን እያደረገ የሚገኘው የታከለ ኡማ አስተዳደር ጎን ለጎን “ሕገ ወጥ ናቸው” ያላቸውን ቤቶች በተለያዮ አካባቢዎች በማፍረስ ዜጎችን ሜዳ ላይ መበተኑ የከንቲባው እንቅስቃሴ የታይታ መሆኑን ያሳያል በሚል እየተተቸ ይገኛል።
ቀደም ሲል የሰብኣዊ መብት ተሟጋችና ጋዜጠኛ በመሆን የተለያዮ ዓለም ዐቀፍ ሽልማቶችን ደጋግሞ የወሰደው እስክንድር ነጋ በቅርቡ በመሰረተው ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አማካይነት ይህንን የከተማ አስተዳደሩን የቤት የማፍረስ ተግባር በእጅጉ ሲኮንን ነበር።
በተለይም ኮልፌ አካባቢ ያሉ ፈራሽ ቤቶችን ጨምሮ ለተለያዮ ከ100 በላይ ለሚሆኑ አባወራዎች እንባ ብቸኛ ድምፅ የሆነው እስክንድር ነጋ ሰምኑን ቤታቸው ፈርሶ ሜዳ ላይ የተበተኑ ወገኖችን ስፍራው ድረስ ሄዶ ከማፅናናት ባሻገር ድምፃቸውን በተለያዮ መንገዶች እንዲያሰሙ ዕድል ፈጥሯል።
የታከለ ኡማ አስተዳደር የወሰደውን እርምጃ በይፋ የተቃወመውና ቤቶቹ መፍረስ ቢኖርባቸው እንኳን ጊዜው አለመሆኑን የገለጸው እስክንድር ነጋ ዛሬ ማለዳ ከቤቱ ከወጣ በኋላ ፖሊሶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመተላለፍ እንድትታሰር ትዕዛዝ ወጥቶብሃል በሚል ይዘውት ሄደዋል::
ሁኔታውን ለማጣራት ወደ ስፍራው የተጓዘው የአዲስ አበባው የኢትዮጵያ ነገ ዘጋቢ እስክንድርን አግኝቶ መረጃ ለማግኘት ለፖሊሶች ያቀረበው ጥያቄ በዕለቱ የጣቢያ ጠባቂ ፖሊሶች ተቀባይነት ማግኘት አልቻለም ነበር።
የፖሊስ ሃይል እስክንድርን ከሰአት በኋላ የለቀቁት ሲሆን የተሰጠው ምክንያትም ከበላይ በመጣ ትእዛዝ ነው መባሉ አግራሞትን ከመፍጠሩም በተጨማሪ አያያዙ ገዢው ፓርቲ የሕዝቡን ምላሽ ለማየት ሆነ ተብሎ የተደረገ ሊሆን እንደሚችል የፖለቲካ ተንታኞች አስተያየት ሰጥተዋል።
እስክንድር ፍራሽና ብርድልብስ እንዲያመጣ ከተጠየቀ በኋላ ነው በድንገት እንዲፈታ የተደረገው።