ከትራንስፖርትና ደረቅ ወደብ አገልግሎት ጋር በተያያዘ መንግሥት የዋጋ ቅናሽ አደረገ

ከትራንስፖርትና ደረቅ ወደብ አገልግሎት ጋር በተያያዘ መንግሥት የዋጋ ቅናሽ አደረገ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በማኑፋክቸሪንግ ኤክስፖርት ዘርፍ ተሰማርተው ምርታቸውን ወደ ውጭ አገር ለሚልኩ አምራቾች ነጻ እና ቅናሽ የትራንስፖርት አቅርቦት ተመቻችቷል ተባለ::

የትራንስፖርት ሚኒስቴር እንዲህ ያለው  ከትራንስፖርትና ከደረቅ ወደብ አገልግሎት ጋር በተያያዘ የተደረገውን ቅናሽ አስመልክቶ በሰጠው መግላጫ ላይ ነው። በመግለጫው ከነጻ እና ቅናሽ የትራንስፖርት አቅርቦት በተጨማሪ  በደረቅ ወደብ አገልግሎት ላይም ለአምራቾቹ ቅናሽ መደረጉን ተረድተናል።

የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ከውድቀት ለመታደግ መንግስት የዘርፉ ተዋንያኖችን የሚያግዝ ውሳኔ ማስተላለፉን ያስታወሱት የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ፣ “ድጋፉ በትራንስፖርትና በሎጂስቲክስ ዘርፍ የደረቅ ወደብ አገልግሎትን ማዕከል በማድረግ የሚሰጥ እንዲሆን ተወስኗል” ብለዋል።

በመሆኑም ከፈረንጆቹ ግንቦት አንድ ጀምሮ ከኢንዱስትሪ ፓርኮችና ከኤክስፖርት ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች የሚወጡትን ምርቶች ፤ ከሦስት እስከ አምስት ወራት ጅቡቲ ወደብ ነጻ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልጸዋል::  ከዚህ በተጨማሪ ከሞጆ ደረቅ ወደብ ላይ በባቡር ለሚጭኑ፣ እንዲሁም በባቡር ለማይመቹ አካባቢዎች ለሚጫኑ የወጪ ዕቃዎች የወደብና የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ቅናሽ እኔደተደረገ አረጋግጠዋል::

የደረቅ ወደብ አገልግሎት ክፍያ በየትኛውም የጭነት ዘርፍ በ50 በመቶ እንዲቀነስ ተደርጓል ያሉት ሚኒስትሯ ከሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ እስከ ሞጆ ደረቅ ወደብ ለሚጓጓዙ ጭነቶች የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ሦስት ተሽከርካሪዎችን መድቦ በ50 በመቶ ቅናሽ አገልግሎት ተወስኗል ሲሉ ገልጸዋል።

በባቡር ለማጓጓዝ አመቺ ያልሆኑ ጭነቶችን ወደ ጂቡቲ የሚወስዱ የማኑፋክቸሪንግ ኩባንያዎች ከባህር ትራንስፖርትና ከትራንስፖርተሮች ጋር በመሆን በ50 በመቶ ቅናሽ እንዲያጓጉዙ መወሰኑን የተናገሩት ወ/ሮ ዳግማዊት፤ ከጂቡቲ ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች ምርታቸውን ለመላክ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ለሚጠቀሙ ላኪ ደንበኞችም ተመሳሳይ በሆነ መልኩ እስከ 73 በመቶ የሚደርስ ቅናሽ መደረጉን አስታውቀዋል።

LEAVE A REPLY