ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ከኮሮና ቫይረስ በሽታ ጋር በተገናኘ ባሰራጩት መረጃ ምክንያት ጋዜጠኞች መታሰራቸው ያሳስበኛል ሲል የኢትዮጵያሰብአዊ መብት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
በቅርቡ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተገናኘ ባሰራጩት መረጃ ምክንያት ሁለት ጋዜጠኞች ከክስ በፊት መታሰራቸው በብርቱ እንደሚያሳስበው ኮሚሽኑ የገለፀው ባለፈው ቅዳሜ በአፍሪካ ከክስ በፊት የሚደረግ እስራትን የመከላከል ቀን ታስቦ መዋሉን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ላይ ነው፡፡
ከክስ በፊት ተይዘው ለረጅም ጊዜ ታስረው የሚቆዩ ሰዎች ጉዳይ በኢትዮጵያ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ የተገለፀ ሲሆን በአፍሪካ የወንጀል ክስ ከመቅረቡ በፊት ሰዎች በፖሊስ ጣቢያዎች፣ በማረሚያ ቤትና በሌሎችም የማቆያ ስፍራዎች ለረጅም ጊዜ በእስር የሚማቅቁ መሆናቸው ተገቢ እንዳልሆነ ተገልጿል፡፡