በአዲስ ማኅበራዊ ውል የምንደራደርበትና የኢፌዴሪ ሕገ መንግስትን የማሻሻያው ጊዜ አሁን ነው!
• ለኢፌዴሪ ጠ/ሚ/ር ዶ/ር አብይ አህመድ
• ለኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ
• ለኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
• ለኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት
• ለመላው የአማራ ሕዝብ
• ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች
• ለተፎካካሪ የፓለቲካ ፓርቲዎች
• ለዓለም አቀፍና አገር አቀፍ ሚዲያዎች
• በአዲስ አበባ ለሚገኙ ለኢትዮጵያ ወዳጅ አገራት ኢምባሲዎች፣ ሚሲዮኖችና ዓለም አቀፍ ተቋማት
ክቡራትና ክቡራን፣
በመላው ዓለም የተከሰተውን የሳምባ ቆልፍ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ተከትሎ በኢትዮጵያም አገራዊ የጤናና የማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ ችግር መሆኑን በመገንዘብ በመጪው ነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ ይካሄዳል ተብሎ ታስቦ የነበረው 6ኛ ዙር አገራዊ ምርጫ በተያዘለት ጊዜ ማካሄድ እንደማይችልና ምርጫውም ላልተወሰነ ጊዜ እንደተራዘመ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡ ይህንን ተከትሎ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በዚህ አመት መጨረሻ የስልጣን ዘመኑ የሚጠናቀቅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ምን ሊደረግ እንደሚችል በሁላችንም ዘንድ የመወያያ አጀንዳ ሆኖ ሰንብቷል፡፡
በኢፌዴሪ ሕገ መንግስትም ሆነ በሌሎች የአገሪቱ ሕጎች ምርጫ ስለማራዘምም ሆነ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የአስፈጻሚውን ስልጣን ማራዘም የሚቻልበት ግልጽ ድንጋጌ የለም፡፡ ስለዚህ ሁኔታው የብሔራዊ የአንድነትና ጊዜያዊ መንግስት የማቋቋም፤ እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብና ሁሉም ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት አዲስ ማኅበራዊ ውል የምንገባበትን ጊዜ አስፈላጊ እንዳደረገው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በጥብቅ ያምናል፡፡ ስለዚህ የኢፌደሪ መንግስት ይህን አጋጣሚ በመጠቀም የሕገ-መንግስት ማሻሻያ ሂደት እንዲያስጀምር አብን ብሔራዊ ጥሪ እያቀረበ መላው የአማራ ሕዝብና ኢትዮጵያዊያን የአብንን ብሔራዊ ጥሪ ደግፋችሁ ለብሔራዊ የአንድነትና የጊዜያዊ መንግስት መቋቋም መሳካትና ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ይሁንታ የሰጡትና ዘብ የሚቆሙለት የተሻሻለ ወይም አዲስ ሕገ-መንግስት እንዲዘጋጅ ለጀመርነው ትግል ከጎናችን እንድትቆሙ ታሪካዊ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ አብን አሁን በስራ ላይ ካለው የኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት ዉስጥ የሚከተሉት 15 አንቀጾች በማሻሻያው እንዲካተቱ በመላው ኢትዮጵያዊያንና በአማራ ሕዝብ ስም ለመንግስት ይፋዊ ጥሪዉን ማስተላለፍ ይወዳል፡፡ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) መሻሻልና መቀየር ያለባቸው የሕገ መንግስቱ አንቀጽ ናቸው ብሎ ያስጠናቸውና የለያቸው የሚከተሉት ናቸው፡፡
መግቢያ:- «እኛ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች» የሚለው መግቢያውና ስያሜው ገጽ ላይ ያለው ጥርት ያለ ትርጉም የሌለው በሶሻሊስታዊ እሳቤ የተቃኘ አገላለጽ አገራዊ አንድነትን ሊገልጽ፣ ከልዩነት ይልቅ አንድነትን ሊያጎላ በሚችል «የኢትዮጵያ ሕዝብ» በሚል አገላለጽ መተካት አለበት። በቋንቋና ኃይማኖት የተለያዩ ሕዝቦች ያሏቸው አገራት ሳይቀሩ የሕገ-መንግስታቸውን መግቢያ «እኛ የዚህ አገር ሕዝቦች..» ብለው ይጀምራሉ። ለምሳሌ የደቡብ አፍሪቃና አሜሪካ ሕገ መንግስቶችን ማየት ይቻላል።
አንቀጽ 3:- የኢትዮጵያ ሰንደቀላማ ላይ ምንም አይነት አርማ ሊቀመጥበት አይገባም። ይህ ከአባቶቻችን የወረስነው፣ ለልጆቻችን የምናወርሰው፣ አባቶቻችን የሞቱለትና እኛም የምንሞትለት ሰንደቅ አላማ ምልዑ የሆነ ነው። የሕዝቦችን ተስፋ ለማመልከት ቢጫውን ቀለም፥ የኢትዮጵያን ሕዝብና የኃይማኖቶችን እኩልነት ለማመልከት የሶስቱ ቀለማት እኩልነትን መጠቀም ይቻላል።
አንቀጽ 5፡- አማርኛ የፌደራል መንግስቱ የስራ ቋንቋ ብቻ ሳይሆን የአገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ መሆን መቻል አለበት። አማርኛ ቋንቋ ኢትዮጵያን ካስተሳሰሩ ነገሮች መካከል አንዱና ዋነኛው ክር ነው። ስለዚህ አማርኛ ቋንቋ የፌደራል መንግስቱ ስራ ለመስራት ወይም አገልግሎት ለመስጠት የሚጠቀምበት ቋንቋ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ሕዝብ ሁኖ ሁሉም ክልሎች የሚያሳድጉት፣ የሚያጎለብቱት፣ የሚጠቀሙበት ብሔራዊ ቋንቋ መሆን አለበት። አማርኛ ብሔራዊ ቋንቋ ባለመሆኑ የተነሳና የፌደራል መንግስቱ የስራ ቋንቋ ብቻ በሚል በመጠቀሱ የተነሳ በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ላይ ተፅዕኖ እያደረሰባቸው ይገኛል፤ በዚህም በተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ አማራዎችም ቋንቋቸውን እንዳይጠቀሙ እየተደረገ ነው። ለዚህ ምሳሌ በኦሮሚያና ትግራይ ክልሎች በአማርኛ ቋንቋ የተጻፉ የንግድ ታፔላዎች ላይ የሚደርሱ ማቅለሞች እና ማፍረሶች አስረጂዎች ናቸው።
አንቀጽ 8፡- ላይ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። አንድ የኢትዮጵያ ሕዝብ መኖሩን ያመላክታል። ይህ ማዕከላዊነትን ወይንም ወደ አንድ መጨፍለቅን አያሳይም፡፡ አለበለዚያ ጉዳዩ የፌደሬሽን ሳይሆን የኮንፌደሬሽን ይሆናል ማለት ነው፡፡
አንቀጽ 39:- መገንጠል መሠረታዊ የሆነው የፌደራሊዝም ጽንሰ ኃሳብ ማለትም የድርድር ጉዳይን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ተግዳሮት ነው፡፡ መገንጠል ከፌደራሊዝም ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም፤ መገንጠል ያልሰለጠነ ድርድርን ይጋርጣል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ሊሰጠው ይገባል፤ ነገር ግን የመገንጠል መብት ሊሰጠው አይገባም። ይህ የመገንጠል ጽንሰ ኃሳብ ያለምንም ሁኔታዎች (Conditions) በሕገ መንግስት ማዕቀፍ ውስጥ ማካተት የአገሪቱን ሉዓላዊ አንድነት ለአደጋ ማጋለጥ ነው።
ከአንቀጽ 45 በኋላ ስላሉ አንቀጾች፡- አገሪቱ የፌደራል መንግስት አወቃቀር ልትከተል ትችላለች። ነገር ግን ክልሎች ሲዋቀሩ አንድን ክልል ለአንድ ብሔር የመስጠት አካሄድን ሊያስቀር በሚችልና በክልሎች መካከል የሕዝብ ብዛትና የእድገት ልዩነትን በአመጣጠነ መልኩ ታሪክንና መልከዓምድራዊ አቀማመጥን፣ የሕዝብ አሰፋፈርንና ቋንቋን ወዘተ. መስፈርቶች ባማከለ መጠን ለአገሪቱ አንድነትና ለሕዝብ ሰላማዊ መስተጋብር መሠረት በሚጥል መልኩ መሆን አለበት።
በአንቀጽ 47 መሠረት የተቋቋሙ ክልሎች መፍረስ አለባቸው። አሁን ያለው የክልሎች አወቃቀር የአማራን ሕዝብ ታሪካዊ ግዛቶች የከፋፈለና የአማራን ሕዝብ የማንነት፣ የቋንቋ፣ የባኅል፣ የሕይዎት፣ የኢኮኖሚ ወዘተ. መብቶች የማያስከብር ነው። ለምሳሌ ከላይ በጠቅላላው ክፍል በተጠቀሰው መልኩ መተከል የሚባለው የቤንሻንጉል ክልል ግዛት አማራ የሚበዛበት በታሪክም የአማራ ሕዝብ መኖሪያ የሆነ ቀየ የፌደራሉ ሕገ መንግስት እውቅና ለሰጠው የቤንሻንጉል ክልል ተሰጥቷል። ይህ የቤንሻንጉል ክልል ደግሞ በሕገ መንግስት የአማራን ሕዝብ የክልሉ ባለቤት አይደለም ብሎ ደንግጓል። በዚህ መሠረት ቤንሻንጉል ክልል ውስጥ የሚኖር የአማራ ሕዝብ አገር እና ዕርስት አልባ ነው ማለት ነው። ይህ አካሄድ ሌሎች ክልሎች ውስጥም አለ። ለምሳሌ፦ የሃረሪ ክልል ባለቤት የሃደሬ ሕዝብ ነው። ነገር ግን አማራ በክልሉ ውስጥ በቁጥር ይልቃል። ይህ በቁጥር የሚልቅ ሕዝብ ምንም አይነት የባለቤትነት መብት የለውም ወይም ከሕዝቡ በኋላ በመጣ የፌደራልና የክልል ሕገ መንግስቶችና ሕጎች የተነሳ አገር እና መብት አልባ ሁኗል። ይህ የክልል ባለቤትነትን ለአንድ ወይም ለተወሰነ ቡድን መስጠትና የአማራን ሕዝብ አገር አልባ ማድረግ በክልሎች ውስጥ በኢኮኖሚም ሆነ በፓለቲካው እንዲገፋ የሚያደርግ አካሄድ ነው።
ሌላው ደግሞ የአማራ ክልል ሕገ መንግስት የክልሉ ባለቤቶች ብሎ የጠቀሰው በክልሉ የሚኖረውን ሁሉንም ሕዝብ ነው። ሌሎች ክልሎች ደግሞ የክልሉ ባለቤት ብለው ያስቀመጡ ወክለነዋል የሚሉትን ሕዝብ ብቻ ነው። ስለዚህ አንድ በኦሮሚያ ክልል ተወልዶ ያደገና የሚኖር አማራ አገር አልባ ነው ማለት ነው። ምክንያቱም አማራ ክልል ስለማይኖር የአማራ ክልል አገሩ ወይም ክልሉ አይደለም፤ ኦሮሞ ስላልሆነ ደግሞ የኦሮምያ ክልል ክልሉ ወይም አገሩ አይደለም። ይህ ሰው አገር አልባ ነው ማለት ነው፤ ስለዚህ እንዲህ አይነት ሁኔታዎችን ለማስቀረት ክልሎች መፍረሳቸው የግድ ነው።
አንቀጽ 49፡- ላይ የፌደራል መንግስት ዋና ከተማዎች አዲስ አበባና ድሬደዋ መሆን አለባቸው። ምንም እንኳ ድሬደዋ የከተማ አስተዳደር ሁና ብትቋቋምም እየተዘወረች ያለችው ግን በሶማሌዎችና በኦሮሞዎች ነው (40%-40%-20% የሚለውን ሕግ ልብ ይሏል)። ይህ ማለት አብላጫ ቁጥር ያለው የአማራ ሕዝብና ሌላው ሕዝብ ምንም አይነት የፓለቲካ ውክልና የላቸውም። ይህ የፖለቲካ ውክልና ማጣት በሌሎች መብቶች ላይ የሚያመጣውን ተጽዕኖ መገመት ቀላል ነው። ድሬደዋ የብዙ ብሔረሰቦች መገኛ እንደመሆኗ መጠን የሶማሌና የኦሮሞ ፖለቲከኞች እርስ በእርስ የሚጓተቱባት ከተማ ስለሆነች፣ የፈደራል መንግስቱ ዋና ከተማ በአንድ ቦታ ላይ ብቻ መንጠልጠ imbalance እያመጣ ስለሆነ፣ አብላጫ ቁጥር ያለው ኦሮሞና ሶማሌ ያልሆነው የድሬደዋ ሕዝብ እየተበደለ ስለሆነ እና የፌደራል መንግስቱ የራሱ የሆነ territory ሊኖረው ስለሚገባ ድሬደዋ ከተማ ከአዲስ አበባ ጋር አብራ በሕገ መንግስት የፌደራል መንግስት ዋና መቀመጫ መሆን አለባት።
አንቀጽ 49/5፡- የኦሮምያ ክልል ልዩ ጥቅም ይከበርለታል የሚለው አንቀጽ ሊወጣ ይገባል። ምም እንኳን ይህ አንቀጽ ባብዛኛው ባለተገባ መረዳት ላይ አተኩረን እንድናየው እየተደረገ ቢሆንም /ማለትም ሕገ መንግስቱ የኦሮሚያን ጥቅም በተመለከተ ከሰርቪስና ከአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ጋር በተመለከተ መሆኑን መገንዘብ የግድ ነው/ ነገር ግን አንድምታው በራሱ አግባብ አይደለም፡፡ ስለዚህ ይህ አንቀጽ ሊስተካከል ይገባል፡፡
አዲስ አበባና ድሬደዋ ከተማ የፌደራል መንግስት መቀመጫ ሁነው በዙሪያቸው ካለው ሕዝብ ጋር ጥቅምና ግዴታን እየተጋሩ አንድ አገር እስከመሆናቸው ድረስ አብረው ሊቀጥሉ ይገባል እንጂ አንድ ሕዝብ በአዲስ አበባ ወይም በድሬደዋ ዙሪያ ስላለ ብቻ ልዩ ጥቅሙ ይጠበቅለታል የሚለው አበባል arbitrary discrimination የሚያመጣ አካሄድ፣ አገራዊ እሳቤን የሚያጠፋ መንገድ እንዲሁም ለሌሎች ጥያቄዎች Pandora’s box የሚከፍት ነው። በዚህ አካሄድ ከሄድን እንደአገር ማሰብ እናቆማለን፤ ለዋና ከተማዎች አገልግሎት የሚሰጡ ክልሎችና ቦታዎች ምንም ያህል ሩቅ ቢሆኑ ልዩ ጥቅም ማግኘት አለባቸው ማለት ነው። ለምሳሌ በአዲስ አበባና ድሬደዋ ዙሪያ ከሚኖረው አካባቢ ውኃ ስለሚሄድ ልዩ ጥቅም ከነዚህ ከተማዎች ማግኘት ይጠበቅበታል የሚባል ከሆነ ከተከዜ ወይም ከግልገል ጊቢ ወይም ከጣና በለስ ለዋና ከተማዎች መብራት ስለሚሄድ እነዚህ የኃይል ማመንጫዎች የሚገኙባቸው ሕዝቦች ልዩ ጥቅም ከዋና ከተማዎች ማግኘት አለባቸው ልንል ነው፤ ወይም ደግሞ የመብራት ፖሉ አቋርጧቸው የሚያልፋቸው ቦታዎች በሙሉ ከዋና ከተማዎች ልዩ ጥቅም ማግኘት አለባቸው ወደሚል ጉዳይ ውስጥ ሁሉ ይከታል። ስለዚህ እንደአንድ አገር ሕዝብ ለማሰብ እንዲህ አይነት «የልዩ ጥቅም» እሳቤዎች ከሕገ-መንግስቱ ሊወጡ ይገባል።
አንቀጽ 54/2፡- የምርጫ ስርአቱን በተመለከተ ከላይ የቀረበው አቋም እንደገና ሊጸድቅ ይገባዋል፡፡ የተቀመጠው የምርጫ ስርዓት First Past the Post ወይም Winner take all የሚለው ነው። ይህ ደግሞ አሁን ባለው የፌደራሊዝም አወቃቀር ከአማራ ክልል ከሚባለው ውጭ ያለውን የአማራ ሕዝብ ፓለቲካዊ ውክልና እንዳይኖረው፣ እንዳይመርጥና እንዳይመረጥ ወይም ቢመርጥም ትክክለኛ ውክልና እንዳይኖረው የሚያደርግ አካሄድ ነው። ይህ ጉዳይ በትንሹም ቢሆን ጠቅላላ የሚለው ክፍል ውስጥ ተነካክቷል። ስለዚህ ይህ የምርጫ ስርዓት በProportional Representation (PR) የምርጫ ስርዓት መተካት አለበት። ከPR ወስጥ ደግሞ Party List System የሚባለው የምርጫ ስርዓትን የምንከተል ከሆነ መራጮች ለግለሰብ ሳይሆን ለፓርቲ ድምጻቸውን ይሰጣሉ። ለምሳሌ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) በመላ ኢትዮጵያ ለምርጫ ይሳተፋል። በመላ ኢትዮጵያ ያመጣው ድምጽ በፕርሰንት ይሰላና ያን ያህል የፓርላማ ወንበር ለአብን ይሰጠዋል ማለት ነው። ለምሳሌ አብን በመላ ኢትዮጵያ ያገኘው ከተሰጠው ድምጽ ውስጥ 30% ከሆነ ፓርላማው ውስጥ 30% ወንበር ይኖረዋል ማለት ነው። ስለዚህ በየትኛውም ቦታ የሚገኙ አማራዎች ብዛታቸው ሳያሳስባቸው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን ወይም ሌላ የአማራ ፓርቲን መምረጥ ይችላሉ፣ ድምጻቸውም ባክኖ ሳይቀር ወደፓርላማ ወንበርነት ይቀየራል፤ የፓለቲካ ውክልናም ይኖራቸዋል ማለት ነው።
አንቀጽ 61:- የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት ከእያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብ ከሚወከሉ ይልቅ እኩል ውክልና ባለው አግባብ የክልሎች ተወካዮች ስብስብ ቢሆን፣ የክልሎችና የፌደራል መንግስቱን ስልጣን balance ለማድረግ የሚያስችል ስልጣን መሰጠት አለበት። ስለዚህ አዲስ የሚቋቋሙት ክልሎች እኩል የሆነ የተወካይ ቁጥር በላይኛው ምክር ቤት ሊኖራቸው ይገባል።
አንቀጽ 62/1 እና አንቀጽ 83፡- ሕገ-መንግስቱን የመተርጎም ስልጣን ገለልተኛና ነጻ ለሆነው ፍርድ ቤት እንጂ የፓለቲካ ወገንተኝነት ባለው ስብስብ በሆነው የላይኛው ምክር ቤት ሊሰጥ አይገባም። ምንም እንኳ በሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ኮሚቴ የሚደገፍ ቢሆንም ሕገ መንግስታዊ ትርጓሜዎችን አስመልክቶ የመጨረሻ ስልጣን ያለው የፌደሬሽን ምክር ቤት ነው። ይህ ምክር ቤት ደግሞ ሕግን ለመተርጎም ሕጋዊ እውቀት እንዲሁም ፍትኃዊና ነጻ ውሳኔ ለማስተላለፍም ከወገንተኝነት የጸዳ አቋም የለውም።
አንቀጽ 51(14) እና 55(16)፡- በሰፈረው መሠረት የፌደራል መንግስት ያለአግባብ በክልሎች የሚገባበት ሁኔታ አለ፡፡ ይህንንም ዝርዝር ሕግ በማውጣት ጭምር በተለይም የፌዴራል መንግስት በክልል ጉዳዮች ጣልቃ የሚገባበት ሥራዓት ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁ 359/1995 በሚል ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአገሪቱ ለተነሱ የጸጥታ መደፍረስ ይህ ሕግ ያለአግባብ እየተመነዘረ በመተግበሩ የክልሎችን ልዕልና (autonomy) በእጅጉ ሸርሽሯል፡፡ በተለይም የፌዴራል መንግስት በጸጥታ መድፈረስ፤ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ለመካላከል እና ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ለማዳን በሚሉ ምክንያቶች ጣልቃ ይገባል። ይህም ክልሎች በክልል ጉዳይ እንኳን ስልጣን እንዳይኖራቸው ጠፍንጎ በመያዝ ተለጣፊ እና ጥገኛ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡
አንቀጽ 55(14) እና 55(15) ፡- የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አሰራራቸው በፓርቲ ማዕበል መጠለፉ፡፡ በአገሪቱ የሕዝብ ተቆርቋሪ ተቋማት (public watchdog institutions) አሰራራቸውን ጨምሮ አካሄዳቸው በገዥው ፓርቲ መረብ መጠለፋቸው፤ በተለይም የሁለቱ ተቋማት ዋና ኮሚሽነሮች በጠቅላይ ሚኒስቴሩ አቅራቢነት መሾም በገለልተኝነታቸው ላይ ጥላ እንዲያጠላ ያደረጋል፡፡
አንቀጽ 93፡- በሕገ መንግስቱ ውስጥ አገሪቱ ያጸደቀቻቸው ድንጋጌዎችን በተመለከተ የተገለጸው በግልጽ ዓለም አቀፍ ሕግ ደረጃ የያዙ ልማዶችንም በግልጽ ማካተት ይኖርበታል፡፡ የማይገረሰሱ መብቶች (non-derogable rights) ዝርዝር ውስጥ በሕይወት የመኖር መብትን (the right to life) ማከተት አለበት፡፡ በቅርቡ እንኳን በታወጁ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ወቅት በርካታ ንጹህን የአማራ ብሔር ተወላጆች ሰለባ ሆነዋል፡፡ ይህም ኢትዮጵያ ፈርማ ካጸደቀችው ዓለም አቀፉ የሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን (International Covenant on Civil and Political Rights/ICCPR) አንጻር እንደገና መታየት ያለበት ነው፡፡
ሰላም፣ እኩልነት፣ ነጻነት እና ወንድማማችነት ለኢትዮጵያዊያን ሁሉ ይሁን!
አንድ አማራ ለሁሉም አማራ፤ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!