ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ስመ ገናናዎቹ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እነ ደራርቱ ቱሉ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ስለሺ ስህን እና ሌሎች ታዋቂ ኢትዮጵያውያንን አትሌቶች ጨምሮ የዓለምን ሕዝብ በያለበት ሊያስሮጡ መሆኑ ተሰማ፡፡
ኮሮና ቫይረስ በዓለም ዙሪያ የፈጠረውን የጤና ፈተና ለመቀነስ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዓለም ያሉትን ወገኖች የሚያሳትፍ የኢንተርኔት መላ (ሩጫ) አዘጋጅተዋል ነው የተባለው፡፡
በገዳዮ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሥራቸውን ያጡ፣ በዓለም ጭንቀት እና ሌላም ቀውስ የተፈጠረባቸው በሙሉ በኢንተርኔት የታገዘው ሩጫ እንደሚረዳቸው ነው የታመነበት፡፡
ይህ በኢንተርኔት የሚታገዘው የቨርቹዋል ሩጫ በአትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባ እና በሌሎችም አትሌቶች እንደሚመራ በዩናይትድ ስቴትስ፣ የዋሽንግተን ዲሲ ግራንድ አፍሪካ ራን አዘጋጆች ገልጸዋል፡፡
ፕሮግራሙ ግንቦት 8 የሚካሄድ ሲሆን፤ በአውሮፓ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከለመዱት የአኗኗር ዘይቤ በተለየ መልኩ ረዘም ላለ ጊዜ በቤት ለመቀመጥ በመገደዳቸው ይሄ መላ ያግዛል ነው የተባለው::
በሀገር ውስጥ ሆነ በውጪው ዓለም ያሉ ወገኖች በተለይም ወረርሽኙ በበረታባት የአሜሪካ ምድር የኢትዮጵያ ቨርቹዋል ሩጫ እንደሚጠቅም የገለፁት አዘጋጆቹ ፤ በዝግጅቱ እነዚህ ስመ ጥር አትሌቶች በያሉበት ሆነው በቪዲዮ ተራ በተራ እየሮጡና ዱብ ዱብ እያሉ ያሳያሉ ፣ ሕዝብንም ያነቃቃሉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ለዚህ ፕሮግራም በተዘጋጀ “ዙም ” በተሰኘ መተግበሪያ ላይ በቀጥታ በማኀበራዊ ሚዲያ ከተሳታፊዎች ጋር የሚሮጡ ሲሆን፤ ተሳታፊዎች በቤት ውስጥ፣ ወይም በግቢ ውስጥ አልያም በመሮጫ ማሽን ከአትሌቶች ጋር ይሮጣሉ ፡፡ ሁሉን ኢትዮጵያዊ በዓለም ላይ በሚያሰባስብ የሩጫ ወይም የሶምሶማ ዝግጅት ላይ ተሳታፊዎች በስልካቸው በኮምፒዩተር ወይም ባመቸ ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ፣ዝግጀቱን መከታተል እንደሚችሉ አዘጋጆቹ አስታውቀዋል፡፡