ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የዓለም የገንዘብ ድርጅት (IMF) ሥራ አስፈፃሚ ቦርድ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል
ቦርዱ ኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እንዲረዳት በሚል ነው የ411 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ያፀደቀው። የአይ ኤም ኤፍ ቦርድ ያሳለፈው ይህ ውሳኔ፣ ኢትዮጵያ በፍጥነት የኮሮና ወረርሽኝን ለመግታት የያዘችውን ዕቅድ ለመደገፍ መሆኑም ተሰምቷል።
“ኢትዮጵያ የእዳ ስረዛ ተጠቃሚ ትሆናለች” በማለት ድርጅቱ ትናንት ባወጣው መግለጫ ላይ ይፋ አድርጓል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም ለዓለም ዐቀፉ የገንዘብ ድርጅትና የድርጅቱ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂ የቫን ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
”የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ቦርድ በድርጅቱ ፈጣን የገንዘብ ድጋፍ አሠራር ማዕቀፍ አማካኝነት ለኢትዮጵያ በእጅጉ የሚያስፈልጋትን 411 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አድርጓል። ይህም ኢትዮጵያ በዘርፉ የሚያስፈልጋትን የገንዘብ መጠን መቶ በመቶ የሚሸፍን ነው” ሲሉ ተናግረዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ።