ኢትዮጵያ ነገ ዜና || መንግሥት ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተላለፉ 23 ተከሳሾች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተሰማ:: መረጃውን ይፋ ያደረገው በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የቦሌ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ሲተላለፉ ያገኘኋቸውን 23 ተከሳሾችን ይዤ በፍርድ ቤት አስቀጥቻለሁ፡፡
የቦሌ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወንጀልና የትራፊክ አደጋ ምርመራ ዲቪዚዮን ሓላፊ ኢንስፔክተር ያሬድ ታረቀኝ፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ የተደነገጉ ጉዳዮችን ጥሰው የተገኙ፣ 852 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር በማዋል 789 ያህሉ በክ/ከተማው በተዋቀረው ግብረ ኃይል በምክርና በተግሳፅ እንዲታለፉ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
ሺሻ በማስጨስ፣ ጫት በማስቃም፣ ኢንተርኔትና ቪዲዮ ቤት ውስጥ ተሰብስቦ በመገኘት፣ ፑል ቤት መሰባሰብ፣ በቁማር ቤቶች በመገኘት፣ መጠጥ መሸጥና ተሰብስቦ መገኘት፣ ርቀትን ሳይጠብቁ መገኘትን የመሳሰሉት ጥፋቶች ግለሰቦቹ የተያዙበት ምክንያት ነው ተብሏል፡፡ በመኪና ውስጥም ተሰባስበው አልኮል መጠጥ ሲጠጡ በመገኘታቸው በቁጥጥር ስር የዋሉ መኖራቸው ተነግሯል፡፡
በተለይም ከአዋጁ ጋር ተያይዞ የሚፈፀሙ ጥፋቶችን በአጥፊዎች ላይ አፋጣኝ ውሳኔ እንዲሰጥ ከፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ቦሌ ምድብና ከፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ ጋር እየሠራ መሆኑን የጠቆሙት የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ ጽ/ቤት ም/ሓላፊ ወ/ሮ ትዕግስት ቢሻው፤ እስካሁንም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማስፈፀም ረገድ በ23 ተከሳሾች ላይ በፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲሰጥባቸውና እንዲቀጡ መደረጉን፣ ቀሪ 29 ተከሳሾች ጉዳያቸውም እየታየ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡