ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ በተከሰሱበት ወንጀል የጥፋተኝነት ውሳኔ ዛሬ ማስተላለፉ ተሰማ።
የጥረት ኮርፖሬሽንን በመመዝበር በአቶ በረከት ስምዖን የክስ መዝገብ የተከሰሱት አንደኛ ተከሳሽ አቶ በረከት ስምዖን፣
ሁለተኛ ተከሳሽ አቶ ታደሰ ካሳ እና ሦስተኛ ተከሳሽ አቶ ዳንኤል ግዛው ፤ በዐቃቤ ሕግ በተመሠረቱባቸው አራት የተለያዮ ክሶች ሲከራከሩ ቆይተዋል።
ሦስቱ ተከሳሾች ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በነበሩ የሥራ ውሎች የጥረት ኮርፖሬትን ጥቅም በሚጎዳ መንገድ ተንቀሳቅሰዋል የሚሉ አራት ክሶች ሲቀርቡባቸው፤ ሁሉም ተከሳሾች ድርጊቱን አልፈጸምንም፤ ጥፋተኛም አይደለንም ሲሉ ክደው መከራከራቸውን ፍርድ ቤቱ ገልጿል።
ይሁን እንጂ ፍርድ ቤቱ ባዋለው ችሎት የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን መርምሮ የጥፋተኝነት ውሳኔ ዛሬ ሰጥቷል። በመሆኑም አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ ጥፋተኛ ሲባሉ ፣ ሦስተኛ ተከሳሽ አቶ ዳንኤል ግዛው ከቀረቡት ክሶች ነፃ እንደሆኑ ተረጋግጧል።