ኦነግ፣ አረናና ኦፌኮን ጨምሮ ሠባት ፓርቲዎች ከመስከረም 30 በኋላ ብጥብጥ ይከሰታል ሲሉ...

ኦነግ፣ አረናና ኦፌኮን ጨምሮ ሠባት ፓርቲዎች ከመስከረም 30 በኋላ ብጥብጥ ይከሰታል ሲሉ አስጠነቀቁ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || “አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት ከመስከረም 30 በኋላ አገርን ማስተዳደር የሚያስችል ሕጋዊ መሰረት ሊኖረው አይችልም” ያሉ ሠባት የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁን ላለው  ሀገራዊ ችግር ምላሽ የሚሰጠው “ፖለቲካዊ መፍትኄ” ነው ሲሉ ገለፁ።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በነሐሴ ወር ለማካሄድ ታቅዶ የነበረውን ምርጫ ማስፈጸም አስቸጋሪ በመሆኑ መንግሥት የምርጫ ጊዜን በማራዘም ምርጫውን ማካሄድ ያስችላሉ ያላቸውን አራት አማራጮች ማቅረቡ ይታወቃል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን መበተን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ፣ ሕገ-መንግሥትን ማሻሻል እና የሕገ-መንግሥት ትርጓሜ መጠየቅ የሚሉት ነጥቦች በአማራጭነት የቀረቡ ናቸው።

እነዚህን የመንግሥት አማራጮች ውድቅ ያደረጉት ሠባቱ ፓርቲዎች፤ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር፣ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ የአገው ብሔራዊ ሸንጎ፣ የሞቻ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ አረና ትግራይ ለሉዓላዊነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ፣ እንዲሁም ከፋ አረንጓዴ ፓርቲ  ሲሆኑ፤ ፓርቲዎቹ መንግሥት ያቀረባቸውን አማራጮች ገምግመን የራሳችንን አቋም ይዘናል ሲሉ የተለየ አቋማቸውን አስታውቀዋል::

“መንግሥት ያቀረባቸው 4 አማራጮች የመንግሥትን የሥራ ዘመን ለማራዘም የሚያስችል ሕገ-መንግሥታዊ መከራከሪያ ማቅረብም አይችሉም” የሚሉት ፓርቲዎቹ “መፍትኄው የኮሮና ቫይረስ ተወግዶ ምርጫ እስክናካሂድ ድረስ የሚፈጠረውን የመንግሥት የሥልጣን ክፍተት ለመሙላት የሚረዳው ሀገራዊ የፖለቲካ ስምምነት ላይ መድረስ ብቻ ነው” ከማለታቸው ባሻገር፤ መፍትኄ ያሉትን በዝርዝር የሚገልፅ ሰነድ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ለማቅረብ ዝግጅታችንን አጠናቀናል ሲሉ ገልፀዋል።

“ከዚህ ውጪ የሚወሰድ ማንኛውም እርምጃ ፖለቲካዊ፣ ሕጋዊና እና ሕዝባዊ ተቀባይነት ስለሌለው አገሪቱን ወደ ከፋ የፖለቲካ ቀውስና ብጥብጥ የሚወስድ ነው የሚል ስጋት አለን” በማለት መጪው ጊዜ የብጥብጥ ሊሆን እንደሚችል ቅድመ ግምታቸውን ያስቀመጡት ሠባቱ ፓርቲዎች፤ ሁሉንም ከሚያግባባ ስምምነት ላይ ለመድረስ፤ ውይይቱ እና ድርድሩ በገለልተኛ አካል እየተመራ፣ በ2012 ዓ.ም ምርጫ ለመሳተፍ የተመዝገቡ ፓርቲዎች ብቻ መሳተፍ እንዳለባቸው እና በድርድሩ የሚደረሰው ስምምነት በሁሉም ወገን ተፈጻሚነት ሊኖረው እንደሚገባም አስረድተዋል።

LEAVE A REPLY