ገቢዎች ሚኒስቴር በኮሮና ምክንያት ለንግድ ድርጅቶች የግብር ዕዳ ስረዛ አደረገ

ገቢዎች ሚኒስቴር በኮሮና ምክንያት ለንግድ ድርጅቶች የግብር ዕዳ ስረዛ አደረገ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የንግድ እንቅስቃሴው የከፋ መስተጓጎል እንዳይደርስበት ለንግድ ድርጅቶች፣ የግብር ዕዳ እስከመሰረዝ የደረሰ ውሳኔ መስጠቱን የገቢዎች ሚኒስቴር ገለፀ፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ዛሬ በሰጠው መግለጫ እስከ 2007 ዓ.ም ወይም በጎርጎሮሳዊያን አቆጣጠር ግብር የሚከፍሉ፣ እስከ 2015 ድረስ የግብር እዳ የነበረባቸው ድርጅቶች የፍሬ ግብር፣ መቀጫና ወለድ ሙሉ በሙሉ ተሰርዞላቸዋል ብሏል፡፡

ከ2008 ወዲህ ያሉና የግብር ውሳኔ የተላለፈላቸው ነጋዴዎች ደግሞ በ30 ቀን ውስጥ የውሳኔውን 25 % ከከፈሉ ቀሪውን 75 % ግብር እስከ አንድ ዓመት  ባለው ጊዜ ቀስ ብለው እንዲከፍሉ የተራዘመላቸው ከመሆኑ ባሻገር  ወለድና መቀጮም ተሰርዞላቸዋል መባሉን ሰምተናል፡፡

የንግድ ድርጅቶቹ በአንድ ወር ውስጥ ሙሉውን መክፈል ከቻሉ ደግሞ አጠቃላይ መክፈል ካለባቸው ግብር ለማበረታቻ 10 % ቅናሽ እንደሚደረግላቸው ተነግሯል፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር የግብር ስረዛና የመክፈያ ጊዜ የማራዘም እርምጃ የወሰድኩት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የንግድ እንቅስቃሴው እንዳይቀዛቀዝ፣ ድርጅቶቹ የቀጠሯቸው ሠራተኞችን ይዘው እንዲቆዩ ፣ እንዲሁም የምርትና የአገልግሎት አቅርቦት እንዳይስተጓጎል በማሰብ መሆኑን አስታውቋል፡፡

መንግሥት ይህን ውሳኔ በማሳለፉ ምን ያህል ገቢ ሊያጣ እንደሚችል እስካሁን የተጠና ጥናት አለመኖሩና ጉዳዮ በጥልቀት እየታየ መሆኑ ተሰምቷል፡፡

LEAVE A REPLY