ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የግል ትምህርት ቤቶች የተማሪዎችን ወርሃዊ ክፍያ በተመለከተ ትምህርት ሚኒስቴር ባስተላለፈው መመሪያ መሰረት እንዲፈፅሙ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አሳሰበ፡፡
ትምህርት ቢሮው ይህን ይበል እንጂ በአዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ በርካታ የግል ትምህርት ቤቶች የኮሮና ቫይረስን ለመቆጣጠር ሲባል ትምህርት ቤቶች ቢዘጉም ወላጆችም ሙሉ ክፍያ እንዲከፍሉ እያስገደዱ ናቸው:: ይህን አሠራር መንግሥት ውድቅ በማድረግ በወጣው መመሪያ መሠረት እንዲተገብሩ የመጨረሻ ነው ያለውን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል::
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ዛሬ በሰጠው ኮስተር ያለ መግለጫ ልጆቻቸውን በግል ት/ቤት የሚያስተምሩ ወላጆች ልጆቻቸው ላልተማሩበት ሙሉ ወርሃዊ ክፍያ እንዲፈጽሙ የሚያስገድዱ ትምህርት ቤቶችን ኅብረተሰቡ በአቅራቢያው ለሚገኙ ለወረዳ እና ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽ/ቤቶች እንዲጠቁሙ ወይም የሕግ አካላት እንዲያሳውቅ ይፋ አድርጓል፡፡