ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከሕጋዊ መንገድ ውጪ ሥልጣን ለመያዝ የሚንቀሳቀሱ ናቸው ያሏቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞችን በከፍተኛ ሁኔታ አስጠንቅቀዋል፡፡
ዶክተር ዐቢይ መንግሥታቸው በሕገ መንግሥቱና በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ካልሆነ በስተቀር የጨረባ ምርጫ ለማድረግ በሚነሱት ላይ ወሳኝ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ ጠቁመው፤ ለዚህም መንግሥታቸው ዝግጁ እንደሆነ አረጋግጠዋል፡፡
ሥልጣንን ያለ ምርጫና ከሕግ ውጪ በሁከትና በብጥብጥ ካልሰጣችሁን፣ ሀገር አተራምሳለሁ የሚለውን ማንኛውንም ሀይል አንታገስም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በሚያደርጉት ቅስቀሳና ክርክር ላይ ወጣቶችንና እናትችን ከሚያጠቃ፣ ቤትና ንብረት ከሚያወድም፣ የትኛውንም ዓይነት ጥፋት ከሚያስከትል ፕሮፐጋንዳ ተቆጥበው በአሳማኝና ተጨባጭ የሐሳብ የበላይነት ላይ እንዲያተኩሩ መክረዋል::
ሰሞኑን ቀጣዮ ሀገራዊ ምርጫ በኮሮና ቫይረስ በታሰበለት ጊዜ ማካሄድ የማይቻል መሆኑን ተከትሎ የተለያዮ ሓላፊነት የጎደላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፍተኛ ውዥንብር እየፈጠሩ መሆኑ እየተገለጸ ሲሆን በትግራይ የመሸገው የህወሓት አመራር በበኩሉ ነሀሴ 23 ምርጫው ካልተካሄደ በትግራይ ክልል ምርጫው እንደሚደረግ ባወጣው መግለጫ አመላክቷል።
በሌላ በኩል ጃዋር መሐመድ፣ ልደቱ አያሌው እና ኢ/ር ይልቃል ከኦነግ፣ አብንና ኦብፓ ጋር ተጣምረው ከመስከረም 30 በኋላ የሽግግር መንግሥት መመስረት አለበት በማለት ለእነርሱ ሥልጣን ማግኛ የምስኪኑን ኅብረተሰብ ሕይወት በመስዋዕትነት ለመገበር ሰፊ የጥፋት ዘመቻ በማካሄድ ላይ መሆናቸው ተጠቁሟል።