ት/ቤቶች በመዘጋታቸው ያለ ዕድሜ ጋብቻ መጨመሩ ተነገረ

ት/ቤቶች በመዘጋታቸው ያለ ዕድሜ ጋብቻ መጨመሩ ተነገረ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በአማራ ክልል ባሉ የተለያዩ ዞኖች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን ተከትሎ ያለ እድሜ የሚደረጉ ጋብቻዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው ተባለ።

ይህ ለመሆኑ መረጃው አለን ያሉት የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህጻናት እና ወጣቶች ቢሮ ምክትል ቢሮ ሓላፊ ወይዘሮ ሠላማዊት አለማየሁ ፤ በተለይም በአንዳንድ ዞኖች ላይ በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን ገልጸዋል። ከዚህ ቀደም መረጃዎች ይሰበሰቡ የነበረው በዋነኝነት በትምህርት ቤቶች እና ድግሶች ቢሆንም፤ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው፣ ተማሪዎች እና መመህራኖች ስለማይገናኙ፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድግሶች እንዳይከናወኑ በመከልከሉ ምክንያት  የመረጃ እጥረት መከሰቱም ተሰምቷል።

ከኮሮና ቫይረስ ግብረ ኃይል ጋር በመጣመር ቤት ለቤት በሚደረጉ አሰሳዎች ጥቆማዎች እየደረሷቸው መሆኑን ያልሸሸጉት ምክትል ሓላፊዋ፤ በጥቆማዎቹ መሠረት በደቡብ ጎንደር እና ምስራቅ ጎጃም ዞኖች የተንሰራፋ ችግር እንዳለም መረዳታቸውን ጠቁመው፤ “በደቡብ ጎንደር ስማዳ፣ ታች ጋይንት እና ፎገራ ወረዳዎች ላይ ሰፊ የልጅነት ጋብቻን እየተካሄደ እንደሆነ መረጃዎች አሉ። ምስራቅ ጎጃምም በተመሳሳይ ሸበል በረንታ ደባይ ጥላት እና ጎዛምን ወረዳዎች ላይ ሠፊ እንቅስቀሴ አለ” ሲሉ ይፋ አድርገዋል።

በአማራ ክልል ከሦስት ዓመታት በላይ ያለ እድሜ ጋብቻን ለማስቀረት እየተሠራ መሆኑን የጠቀሱት ወይዘሮ ሠላማዊት በበኩላቸው በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር 2019 ብቻ ከ5800 በላይ የልጅነት ጋብቻ የተሰረዘ መሆኑን ገልጸዋል:: በምስራቅ ጎጃም ዞን የተሠማራው ግብረ ሃይል በዞኑ ከ1280 ሠርጎች መታቀዳቸውን አስታውሶ፣ እነዚህን ለማስቆም ጥረት መደረጉን እና በ46 ግለሰቦች ላይም ሕጋዊ እርምጃ ተ መወሰዱን  ገልጿል:: በዞኑ ውስጥ ከፍተኛውን የሚይዘው የደባይ ጥላት ወረዳ መሆኑን የተሰበሰበው በአኃዝ የተደገፈ ማስረጃ ያሳያል።

LEAVE A REPLY