እነ በረከት ስምዖን ይግባኝ እንደሚጠይቁ ጠበቃቸው አረጋገጡ

እነ በረከት ስምዖን ይግባኝ እንደሚጠይቁ ጠበቃቸው አረጋገጡ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የአቶ በረከት ስምዖንና የአቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) ጠበቃ ትናንት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በግለሰቦቹ ላይ የወሰነውን ውሳኔ በመቃወም ደንበኞቻቸው ይግባኝ እንደሚጠይቁ ተናገሩ::

በሌላ በኩል የአቶ በረከት ስምዖን ባለቤት ወ/ሮ አሲ ፈንቴ፤ በባለቤታቸው እና በአቶ ታደሰ ካሣ ላይ የተላለፈው ውሳኔ እውነቱን ለሚያውቅ የሚያሳዝን እና የማይገባ ነው ሲሉ ከመተቸታቸው ባሻገር በብይኑ ማዘናቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

“እንዲህ ዓይነቱ ፍርድ አይገባቸውም፤ በጣም ያሳዝናል። የፍርድ ሂደቱን ከመጀመሪያው ቀድሞ ለተመለከተው የሚደንቅ ነገር አይደለም። የፍርድ ሂደቱ ብዙ መሰናክሎች የነበሩበት እና በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የተፈጸሙበት ነበር” ያሉት የበረከት ስምዖን ባለቤት (ወ/ሮ አሲ) ፤ “በፍርድ ቤት ውስጥ ጩኸት እና ጫጫታ በሚሰማበት ሁኔታ፣ እነ በረከት ሲገቡ እና ሲወጡ እየተሰደቡ፣ ያ ሁሉ የፍትህ እና የጸጥታ አካላት ባሉበት ቦታ በማስፈራሪያ እና በስጋት ተውጠን የነበረውን የፍርድ ሂደት ስናስብ ይህ ዓይነት ውሳኔ ቢወሰን ምንም የሚገርም አይደለም” በማለት የሕግ አስፈጻሚውን  አካል ገለልተኛነት እንደሚጠራጠሩ የጠቆሙበትን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት ባለቤታቸው አቶ በረከትን ካገኙ ከአንድ ወር በላይ እንዳለፋቸው የገለጹት ወ/ሮ አሲ፤ ከፍርዱ ውሳኔ በኋላም በርቀት ነው የተያየነው ብለዋል።

አቶ በረከት እና አቶ ታደሰ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ምን ሊሆን እንደሚችል ገምተው እንደነበር የተጠየቁት ወ/ሮ አሲ፤ “በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ግምት እንዳላቸው አናውቅም። በረከት ግን ምንም መጥፎ ቢሆኑ እንዲህ ይጨክናሉ ብሎ አስቦ አያውቅም” ብለዋል፤ ባለቤታቸው።

“በረከት አያውቃቸውም። 27 ዓመት ሙሉ አብሮ ቆይቶ አያውቃቸውም። በእኔ ግምት እንዲህ ዓይነት ፍርድ ይተላለፍብኛል ብሎ አልገመተም” ሲሉም እርስ በርሱ የሚጣረስ ሐሳብ ሲገልጹ ተደምጠዋል::

የአቶ በረከት ስምዖን እና የአቶ ታደሠ ካሣ ጠበቃ የሆኑት ሕይወት ሊላይ በበኩላቸው ይግባኝ እንደሚጠይቁ ዛሬ ይፋ አድርገዋል።

“በተሰጠው የጥፋተኝነት ውሳኔም ሆነ በቅጣት ውሳኔው ላይ ይግባኝ እንጠይቃለን። ምክንያቱም ብዙ የመከላከያ ማስረጃ አቅርበን እራሳችንን ተከላክለናል ብለን ስለምናስብ ” ያሉት ጠበቃዋ ፤ “ይግባኙ ውድቅ ይሆናል የሚል እምነት የለንም። ምክንያቱም ያቃረብናቸውን ማስረጃዎችን ተመልክቶ ሰሚው ችሎቱ ውሳኔውን ሊያሻሽልላቸው ይችላል የሚል ሙሉ እምነት አለን። እንደውም ነጻ በሚል ያሰናብተናል ብለን ነው የምናምነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ይህ ካልሆነ ግን የፍርዱ ተፈጻሚነት ከባህር ዳር ወደ አዲስ አበባ እንዲዘዋር እንደሚጠይቁ ጠበቃ ሕይወት ከወዲሁ ጠቁመዋል።

LEAVE A REPLY