ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የግብፅ መንግሥት ከሁለት ሳምንት በፊት ሥራ ላይ አውሎት የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይበልጥ የሚያጠብቅ ማሻሻያ እንደጨመረበት ተሰማ።
ማሻሻያው ለሀገሪቱ መከላከያ ሠራዊት፣ የዐቃቤ ሕግ አቻ የምርመራና ክስ የመመስረት ሥልጣንን ጭምር ያጎናፀፈ እንደሆነም ተነግሮለታል::
ግብፅ ከሦስት ዓመት በፊት በሁለት ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያናት ላይ የሽብር ጥቃት ከደረሰ በኋላ በአስቸኳይ ጊዜ አስተዳር ውስጥ ቆይታለች::
የኮሮና ወረርሽኝ እያስከተለባት ያለው ጉዳት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎም አዋጁ ከሁለት ሳምንት በፊት ጠንከር ብሎ እንዲሻሻል ተደርጎ የነበረ ቢሆንም፤ አሁን ደግሞ ለፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ እና ለሀገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ለሦስተኛ ጊዜ ከፍ ያለ ሥልጣን ያጎናፀፈ ሆኖ ፀድቋል።
አዲሱ ማሻሻያ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለመፈፀም መንገድ ያመቻቸ ነው በማለት የመብት ተሟጋቾች እየተቹት ነው ሲል ገልፍ ኒውስ ሲዘግብ፤ መንግሥትም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማሻሻያ የተደረገበት፣ የህዝብን ጤንነት እና ደህንነት ይበልጥ ለማስጠበቅ ነው ሲል ወቀሳውን አጣጥሏል።
በግብፅ እስካሁን ከ8.400 በላይ ሰዎች በኮቪድ19 ቫይረስ ሲያዙ ከአምስት መቶ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ሞተዋል እየተባለ ነው።