የመቀሌ ፋና ኤፍ. ኤም ጋዜጠኞች አ/አ ያለው ዋና መሥሪያ ቤት ጫና አድርጎብናል...

የመቀሌ ፋና ኤፍ. ኤም ጋዜጠኞች አ/አ ያለው ዋና መሥሪያ ቤት ጫና አድርጎብናል አሉ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || መቀሌ በሚገኘው የፋና ኤፍ ኤም ቅርንጫፍ ሬዲዮ ጣቢያ የሚሠሩ ጋዜጠኞችና አመራሮች አዲስ አበባ የሚገኘው የድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤት በሥራችን ላይ ጫና እያደረሰብን ነው ሲሉ ገለፁ።

የመቀሌ ፋና ኤፍኤም 94.8 ሥራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ መሰረት ታደሰ “ፋና ሁለት ዓይነት ፋና ሆኗል፤ በመቀሌና አዲስ አበባ ያሉ አጀንዳዎች ተለያይተዋል።

በሁለቱም የሚሰራጩ ዜናዎችና ዝግጅቶችም የማይገናኙ ሆነዋል”  ያለው የመቀሌ ፋና ኤፍ ኤም 94.8 ሥራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ መሠረት ታደሰ፤ በትግራይ ክልል ስላሉ ጉዳዮች ሳይሆን ከመሃል አገር ለሚመጡ አጀንዳዎች የቅድሚያ ትኩረት መስጠት አለባችሁ በሚል ጫና እየተደረገብን ነው በማለት ኤፍ ቢ ሲን ወቅሷል።

ጋዜጠኞቹና አመራሩ ይህንን አሠራር በመቃወም በተደጋጋሚ ለማስረዳት ቢሞክሩም ከዋናው መሥሪያ ቤቱ በኩል ሰሚ እንዳጡና የድርጅቱን ኤዲቶሪያል ፖሊሲ በማይጥስ መልኩ ለክልላዊና አገራዊ ጉዳዮች ሽፋን መስጠት እንደቀጠሉ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

“ድርጅቱ ኤዲቶሪያል ፖሊሲ፤ እንዲሁም ሌሎች ማንዋሎችና የኢትዮጵያ ብሮድካስት አዋጅ የሚለው ሚድያው 60 ከመቶ ለአገራዊ ጉዳዮች ወይም መረጃዎች ሽፋን መስጠት አለበት። ፋና ግን ላለፉት ሁለት ዓመታት አገራዊ አጀንዳዎችን ወደጎን ትቷል” ያለው ጋዜጠኛ መሰረት፤ “ተቋሙ በአዲስ አበባና በከተማዋ ለሚገኘው የፌደራል መንግሥትን የሚመለከቱ አጀንዳዎች ሽፋን በመስጠት ክልላዊ ጉዳዮችን ረስቷል፤ ይህም የመንግሥት ቃል-አቀባይ ሆኖ እንደማገልገል እንቆጥረዋለን” ሲል ለ25 ዓመታት የህወሓት / ኢሕአዴግ ዋነኛ ልሳን ሆኖ የቆየው ፋና ራዲዮና ቲቪን ገለልተኛ ሚዲያ አድርጎ ለማሳየት የሞከረበትን አስገራሚ አስተያየት ሰጥቷል።

የፋና መቀሌ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ  “በመቀሌም ይሁን በትግራይ ክልል የሚኖሩ ኹነቶች በዜናና በፕሮግራም መልክ ስንልክላቸው አብዛኞቹ እንዲታገዱ፣ ሌሎቹ በተዛባ መልኩ እንዲቀርቡ፣ አልፎ አልፎም እኛ የዘገብነውን ትተው ሌላ ምንጭ የመጠቀም ሁኔታ ይታያል” ሲል መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገውን የዋና መሥሪያ ቤቱን አሠራር ተችቷል።

LEAVE A REPLY