ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑ ነዋሪዎች ለሦስት ወራት ዳቦ የማቅረብ መርሀ ግብር ተጀምሯል ተባለ።
2.000 (ሁለት ሺኅ) ዳቦ አምራቾች ለ 10 ሺህ አባወራዎች በየዕለቱ ከክፍያ ነፃ ዳቦ እንደሚያቀርቡም ተነግሯል። በጎነትን የተመረኮዘው ይህንን መርሀ ግብር ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴና ኢ/ር ታከለ ኡማ ዛሬ በጋራ አስጀምረውታል።
የዳቦ ምገባ ድጋፍ የሚደረግላቸው ቤተሰቦች የተለዩት በየአካባቢው በብሎክ በተደራጁ አስተባባሪዎች ሲሆን፤ ነዋሪዎቹም ለሦስት ወራት በየዕለቱ የዳቦ ድጋፍ ያገኛሉ። ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭቱና ተፅዕኖው ለረጅም ጊዜ የሚቀጥል እንደመሆኑ የተደራጀ ዝግጅት ከወዲሁ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የኮቪድ 19 ቫይረስን ተከትሎ የሚመጡ ችግሮች ብዙ ዜጎችን ለአደጋ የሚያጋልጡ በመሆኑ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብ ባንኮችን በማዘጋጀት ድጋፎችን በማሰባሰብ በኩል እየተወጣ ያለው ሓላፊነት የሚደነቅ ነው ብለዋል ፕሬዝዳንቷ። በአዲስ አበባ ከተማ 1200 የምግብ ባንኮች ተቋቁመዋል።
አሁን በዳቦ የተጀመረው የድጋፍ ትስስር በሌሎች የምግብ አቅርቦቶችም የሚቀጥል ይሆናል ሲሉ የተናገሩት ም/ከንቲባ ታከለ ኡማ፤ ለሦስት ወራት ዳቦውን ለሚያቀርቡት 2.000 ዳቦ ፋብሪካዎች ምስጋና አቅርበዋል።
በሰዐት ሰማኒያ ሺኅ ዳቦ ያመርታል የተባለውና ሙሉ ወጪው በሼኽ ሞሀመድ አልአሙዲ የተሸፈነው የሸገር ዳቦ ፋብሪካ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ወደ ሥራ እንደሚገባ ከንቲባ ታከለ ኡማ በቅርቡ ተናግረው ነበር:: ሆኖም አንዳንድ የመጨረሻ አስፈላጊ ዕቃዎችና የስንዴ ምርት ከውጭ በፍጥነት ለማስገባት ኮሮና እንቅፋት መሆኑን ተከትሎ መንግሥት ለጊዜው ዳቦ ቤቶችን በማስተባበር ድሆችን መመገብ እንዳቀደ ታውቋል።