ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ ተጠቂ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር ስጋቱን አባብሶታል። ባለፉት 24 ሰዐታት ውስጥ 2 ሺኅ 171 ሰዎች ላይ የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጎ በ29 ሰዎች ላይ ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።
ኮሮና ቫይረስ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከልም ሀያ አንዱ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንኪኪ ያላቸው ሲሆኑ፤ ስምንቱ ደግሞ የውጭ ሀገር ጉዞ ታሪክ ያላቸው ናቸው።
በዚህ መሠረት እስካሁን በሀገሪቱ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 239 ደርሷል። ቫይረሱ በላብራቶሪ ምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ሁሉም ወንድ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፤ እድሜያቸው ከ15 እስከ 45 ዓመት የሆኑ ናቸው ተብሏል፡፡
ዛሬ ከተመዘገቡት ሰዎች መሀል ሀያ አንዱ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ናቸው። ቀሪውቹ ሠባት ሰዎች ከሶማሌ ክልል (ከሶማሌ ክልል ለይቶ ማቆያ) እና ከኦሮሚያ ክልል (አዳማ ከተማ በቤት ለቤት አሰሳ እና ቅኝት የተለየ) የተገኙ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡