ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ረጅም ጊዜ በመውሰድ በተለያየ መንገድ ክትትል ሲያደርግበት የነበረው እና በጉዳዩም ላይ በቂ መረጃ ሲያሰባስብበት የቆየው ዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ዝውውር ሥርዓትን በመጠቀም 110 ሚልዮን ዶላር የማጭበርበር እና የዘረፋ የወንጀል ሙከራ በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ።
ተቋሙ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤ ተጠርጣሪዎቹ ነዋሪነቱ አሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት በሆነው ኒል ቻርለስ የተባለ ግለስብ ስም በባንክ የተቀመጠ 110 ሚልዮን ዶላርን የባንክ ሒሳብ ባለቤቱ እንዳዘዘ አስመስለው ሊያወጡ ነበር።
ግለሰቦቹ አዲስ አበባ ከተማ ፊንፊኔ ቅርንጫፍ ተብሎ ከሚታወቀው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተጠቀሰውን ገንዘብ ለማውጣት የተለያዩ የማጭበርበር ስልቶችን ሲያቀናጁ መሰንበታቸውም ተነግሯል።
ሆኖም ሕገ ወጥ የገንዘብ ማዘዋወር እና ዘረፋ ወንጀሉ በብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ክትትል ስር የነበረ በመሆኑ፣ ግንቦት 1 ቀን 2012 ዓ.ም በመጀመሪያ ዙር 60,990,939ብር ከተጠቀሰው ባንክ አውጥተው በማዳበሪያ ጭነው ባዘጋጁት ተሽከርካሪ ሊወስዱ ሲሉ፣ ጥብቅ ክትትል እየተደረገባቸው ስለነበር እዚያው ባንክ ውስጥ እያሉ በፖሊስ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የደህንነት መ/ቤቱ አብረረርቷል።
ወንጀሉን በማቀነባበር ከሚታወቁት መካከል አድይሚ አድርሚ አብዱልራፊ የተባለ ናይጄሪያዊ ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01፣ ሸገር እንግዳ ማረፊያ በቀን 450 ብር እየከፈለ ከአንድ ዓመት በላይ በመቀመጥ ተልዕኮውን ለማስፈጽም ሲንቀሳቀስ እንደነበርም ታውቋል።