ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በጋምቤላ ክልል፣ ደቡብ ሱዳን ድንበር አካባቢ ያለው የሰዎች ዝውውር የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ፈታኝ ሊያደርገው ይችላል ተባለ፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በሁለቱ ሀገሮች መተላለፊያ ድንበር አካባቢ፣ አምስት ያህል ቦታዎች ላይ የሙቀት ልኬት ቢጀመርም ኅብረተሰቡ ከመደበኛ ኬላዎች ውጪ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ክልሉ ከደቡብ ሱዳን ጋር በሠፊው ሰለሚዋሰንና ኅብረተሰቡ በድንበር አካባቢ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን የመከላከሉን ሥራ ፈታኝ ያደርገዋል ነው ያሉት፡፡
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳደር በድንበር አካባቢ በሚገኙ ኬላዎች የፀጥታ ኃይሎች ጥበቃ እያደረጉ ቢገኙም፤ አብዛኛው ቦታ ክፍት በመሆኑ ኅብረተሰቡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በሚፃረር መልኩ በህገ-ወጥ መንገድ የመግባትና የመውጣት ሁኔታ እንደሚስተዋል ጠቁመዋል።
በድንበር አካባቢ ያለው ተጋላጭነት ከፍተኛ ቢሆንም ክልሉ የበሽታውን ሥርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ ይገኛል ብለዋል::
በሁለቱ ሀገሮች መተላለፊያ ድንበር አካባቢ አምስት ያህል ቦታዎች ላይ የሙቀት መለኪያ መጀመሩን የተናገሩት የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ሓላፊ ዶክተር ኡጁሉ ኡጁሉ፤ ኅብረተሰቡ ከመደበኛ ኬላዎች ውጪ የሚንቀሳቀስበመሆኑ የምርመራ ሂደቱን ፈታኝ አድርጎታል ከማለታቸው ባሻገር፤ በሽታው እስካሁን በክልሉ ያልተከሰተ ቢሆንም ወደፊት ቢከሰት እንኳን በድንበር አካባቢዎች የለይቶ ማቆያ ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡
ከደቡብ ሱዳን ከመደበኛ ኬላዎች ውጪ የሚገቡ ሰዎች ወደ ከተማ ከመግባታቸው በፊት በመናኸሪያ አካባቢ በመገኘት የሙቀት ልኬት ምርመራ እያደረጉ ነው፡፡ የፌደራልና የክልሉ ፀጥታ ኃይል በድንበር አካባቢ የሚስተዋለውን የሰዎች ዝውውር ለማስቆም ጥረት እያደረጉ ቢሆንም፤ የድንበሩ መስፋት ለሥራቸው እንቅፋት እየፈጠረ እንደሚገኝ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ መከላከያ ሠራዊት በምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል መሰለ መሰረት ገልፀዋል::