ኢዜማ ኅብረተሰቡን በስሜታዊነት በማነሳሳት ሥልጣን መያዝ እንደማይሻ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ አስታወቁ

ኢዜማ ኅብረተሰቡን በስሜታዊነት በማነሳሳት ሥልጣን መያዝ እንደማይሻ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ አስታወቁ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ባለፈው አንድ ዓመት በኢትዮጵያ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመፍጠር የሚያግዙ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን የፓርቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለፁ፡፡

ብዙዎች “በሳሉ ፖለቲከኛ”  በማለት የሚገልጿቸው ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ  ዛሬ ለንባብ ከበቃው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ ፓርቲያቸው ኅብረተሰቡን በጊዜያዊ ስሜት እያነሳሳ፤ በውስጥ ያለውን ቅራኔ እያፋፋመ፤ በዛ በሚገኝ ዝና ሥልጣን ላይ የመውጣት ፍላጎት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡

“ከዚህ ይልቅ ከምንም በላይ አገሪቱ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንድትሄድ የማድረግ ትልቅ ዓላማን በመያዝ ይህንኑ ዓላማ ለማሳካት እየተንቀሳቀሰን ነው” ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ፤ የኢዜማ መፈጠር በአጠቃላይ የአገሪቱን ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሂደት ለማሳደግ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ጠቁመው ፤ በአሁኑ ጊዜ የፓርቲው ትልቁ ጥንካሬ ማን ሥልጣን ላይ ወጣ? የሚል ሳይሆን ፣ ሥልጣን ላይ የሚወጣበት መንገድ እና የጨዋታ ሕጉ ሕጋዊ መሠረት እንዲኖረው የሚያስችል  የፖለቲካ ሥርዓት ለመፈጠር ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ የፓርቲው ዓላማ መሆኑን ይፋ አድርገዋል፡፡

“ያለምንም ማጋነን ላለፈው አንድ ዓመት በፓርቲዎች ምስረታ እና የእንቅስቃሴ ሂደት እንደዚህ ሠፊ አገራዊ ድርጅት መመስረት መቻላችን ትልቅ ውጤት ነው:: በአገሪቱ ታሪክ ዴሞክራሲያዊነት ቀላል ባለመሆኑ በፓርቲ ደረጃ እንኳ እንቅስቃሴዎችን ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ እየሠራን ነው” በማለት የተናገሩት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ “ፓርቲውን ዴሞክራሲያዊ ማድረግ ከምንም ነገር በላይ ነው። በተቻለ መጠን ዓይንን ኳሱ ላይ በማድረግ ዴሞክራሲያዊነት ባህል እንዲሆን ሠፊ ሥራ እየተሠራ ነው፤ ለዚህ ደግሞበኢትዮጵያ የፓርቲዎች ምስረታ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ክፍት የሆነ በዕውቀት እና በጥናት የሚያምን፤ ለዴሞክራሲ ፍፁም ቁርጠኛ የሆነ ፓርቲ መመስረት ችለናል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡፡

ከበርካታ ምሁራኖች ጋር አብሮ በመሥራት ፣ ከ40 በላይ የፖሊሲ ጥናት በማስጠናት፣ ሠፊ የፖሊሲ መንደፍ ሥራዎች መስራታቸውን የጠቆሙት አንገፋው ፖለቲከኛ፤ “ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ብዙዎች አብዝተው ሲጮኹ ኢዜማ ዝምታን ይመርጣል፤ አይናገርም በሚል ብዙ አለመረዳት አጋጥሞ ነበር” በማለት የአንድ ዓመት የፓርቲያቸውን ውጣ ውረድ ካስታወሱ በኋላ፤ የፓርቲያቸው ዋና ጉዳይ አገር የሚያተራምሱ ሰዎችን በማየት በኅብረተሰቡ ተወዳጅነትን ለማትረፍ አገር የማተራመስ ተግባርን የመቀላቀል ዓላማ  አለመሆኑን አስታውቀዋል፡፡

 

LEAVE A REPLY