ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡- በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ድንበሯን ዘግታ የቆየችው ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት የሚያዋስኗት አዲስ አምስት ኬላዎች በቅርቡ ልትከፍት ነው ተባለ፡፡
የቫይረሱ ሥርጭትን መቆጣጠር ባልተቻለበትና በኢትዮጵያ የተጠቂው ቁጥር እያሻቀበ በሚገኝበት በዚህ ሰዐት አጎራባች ኬላዎቹ ይከፈታሉ መባላቸው በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ግርምት ፣ ስጋትና ድንጋጤን እኔደፈጠረ የተለያዮ አስተያየት ሰጪዎች ለኢትዮጵያ ነገ ገልጸዋል::
ኢትዮጵያ በጋምቤላ፣በቤንሻንጉል፣ በሶማሌ ክልሎች ድንበር ላይ 5 ኬላዎችን በቅርቡ እንደምትከፍት የተናገሩት የኢሜግሬሽን ዜግነትና የወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙጅብ ጀማል ናቸው፡፡
የኬላዎቹ መከፈት ከጎረቤት አገራት የሚገቡ ሰዎችን በአግባቡ ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ያስችላል በማለትሓላፊው ቢገልፁም በርካታ ዜጎች ግን ኬላ ከመክፈት ይልቅ ከአጎራባች ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚያስገቡ ማንኛውንም ኬላዎች መዝጋት ነበር ሲሉ አሠራሩን ተችተዋል::
ኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተነሳ ድንበሯን ዝግ አድርጋ ቆይታለች:: በቅርቡ ይህን በመተላለፍ በህገ-ወጥ መልኩ ከጅቡቲ 22 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ሊገቡ ሲሉ ተይዘው ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ መደረጉም አይዘነጋም::