ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡- ዳግም ምዝገባ ሳያከናውኑ የቀሩና ጊዜው ያለፈባቸው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ለማወቅ የመንግሥት ውሳኔ እየተጠበቀ መሆኑ ተሰማ።
በሀገራችን የሚገኙ ሁሉም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እስካለፈው መጋቢት ወር ዳግም ምዝገባ እንዲያከናውኑ ከዓመት በፊት ተወስኖ ነበር።
በተሰጠው የአንድ ዓመት ጊዜ ዳግም ምዝገባውን ያከናወኑ ድርጅቶች ብዛት 1.783 እንደሆነ የገለፀው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ዳኝነት፤ ይመዘገባሉ ተብለው የተጠበቁት 2.250 ድርጅቶች ቢሆኑም፣ 467 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ዳግም ምዝገባውን ሳያከናውኑ ቀርተዋል ብለዋል።
ሳይመዘገቡ የቀሩት ድርጅቶች ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል? የሚለውን ለማወቅ የመንግሥት ውሳኔ እየተጠበቀ እንደሆነ የጠቆሙት ሓላፊዋ፤ ድርጅቶቹ ዳግም ምዝገባውን እንዲያከናውኑ የተወሰነው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጀቶች አዋጅ መሻሻሉን ተከትሎ እንደሆነም አስታውሰዋል::
የቀደመው አዋጅ በርካታ ችግሮች የነበሩበትና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በነፃነት እንዳይሠሩ ያደረገ ነው በሚል ተተችቷል:: የተሻሻለው አዋጅ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ዳግም ምዝገባውን እንዲያደርጉ ያዘዘ ቢሆንም፣ ቀነ ገደቡ ካለፈ በኋላ ዳግም ምዝገባውን ለማከናወን ወደ ኤጀንሲው የሄዱ ድርጅቶች መኖራቸውም ታውቋል።
ዳግም ምዝገባውን ሳያከናውኑ ከቀሩ ድርጅቶች መካከል በሥራ ላይ የሌሉት ተለይተው፣ ንብረታቸው ተመሣሣይ ዓላማ ላላቸው ሌሎች እንዲተላለፍ ይደረጋል ያለው ኤጀንሲው፤ ስለ ተሻሻለው አዋጅ ባለመስማትና በሌሎች ምክንያቶች ሳይመዘገቡ የቀሩት ጉዳይ ግን በመንግሥት ውሳኔ ይሰጥበታል ብሏል።