ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡- የትግራይ ክልል አስፈላጊውን ሁሉ በማድረግ የራሱን ምርጫ ማካሄድ ይችላሉ ሲሉ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ደብረፂዮን ገብረሚካል አስታወቁ። የብልጽግና ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ምላሽ ሰጥተዋል።
ዶ/ር ደብረጽዮን በበኩላቸው የትግራይ ክልል በምርጫና በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ ስለሚያደርገው እንቅስቃሴ መግለጫ የሰጡት ርዕሰ መስተዳደሩ፤ “የፌዴራል መንግሥት ምርጫ ሊያካሂድ እንደማይችል በማስታወቁ በክልል ደረጃ ግን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን እየተከላከልን እኛ በጥንቃቄ ምርጫውን ማካሄድ እንችላለን።
በክልላችን ምርጫው በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ በክልሉ ካሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከማኅበራትና ከሕዝብ ጋር በመመካከር የምርጫ ቦርድንም ባሳተፈ ሁኔታ ሕጋዊ አፈፃፀም እንዲኖረው ይደረጋል” ሲሉ ተደምጠዋል።
የትግራይ መንግሥት በክልል ደረጃ ምርጫ ለማካሄድ የወሰነው ለኮሮና ቫይረስ ትኩረት ባለመስጠት ሳይሆን፣ ለሕዝብ ውሳኔና ለሕገ መንግሥቱ ተገዥ በመሆናችን ነው ብለዋል ዶክተር ደብረፂዮን።
ከቀጣዮ መስከረም በኋላ በየትኛውም ደረጃ ሥልጣን ላይ ያለው የመንግሥት መዋቅር ሕጋዊነት ስለማይኖረው ምርጫ ሳይካሄድ ከቀረ አደገኛ ሁኔታ ሊከሰት ይችላል ያሉት ዶክተር ደብረፂዮን፤ “ምርጫን ማካሄድ የሚያስፈልገው የዜጎችን የመምረጥና የመመረጥ መብትን እንዳይጣስ ለማድረግ ነው።
አሁን ያለው ሁኔታ ምርጫን የማራዘምና ያለማራዘም ብቻ ሳይሆን የሕዝብን ውሳኔ አለመተግበር፣ ሕገ መንግሥቱ ያለማክበር ነው” በማለት የህወሓትን ወቅታዊ ፍላጎት አንፀባርቀዋል።
“ምርጫ አይካሄድም እየተባለ ያለው በኮሮና ቫይረስ ምክንያት አይደለም፤ ቀደም ሲል ፍላጎትና ዝግጅት ቢኖር ኖሮ በግንቦት ወር ላይ ማድረግ ይቻል ነበር” ሲሉም በመንግሥታዊው ብልፅግና በኩል ቀድሞውኑም ምርጫ ለማድረግ ፍላጎት እንዳልነበር ርዕሰ መስተዳደሩ አስታውቀዋል።
“ከምርጫ ጋር ተያይዞ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የሚተረጎም ነገር የለም፤ አምስት ዓመት ማለት አምስት ዓመት ነው” ሲሉም የትርጉም ጥያቄ የቀረበበትን ሁኔታ ውድቅ ያደረጉት ዶክተር ደብረፂዮን፤ ከዚህ ይልቅም ሕገ መንግሥቱን በጣሰ መንገድ ሥልጣንን ለማራዘም የተለያየ ሰበብ ከማቅረብ፣ ከሕዝብና ከፖለቲካ ፓርቲዎች እንደዚሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት መፍትኄ መሻት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ ባለስልጣን አቶ አወሉ አበዲ ጉዳዩን አስመልክተው ለዶቼ ወሌ በሰጡት ቃል ማንኛውም ክልል ለብቻው ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል ገልጸው የትግራይ ክልል ምርጫ ማድረግ አይችልም። ከደረገም መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳል ሲሉ አሳስበዋል