ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡- ፌሊሲዬን ካቡጋ፤ በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ወንጀል እጅጉን ተፈላጊ የነበሩት ፌሊሲዬን ካቡጋ፤ ከሀያ አምስት ዓመት በኋላ በቁጥጥር ሥር ዋሉ::
ወንጀለኛው ፈረንሳይ ውስጥ መያዛቸውን ያረጋገጠው የፈረንሳይ ፍትህ ሚኒስቴር፤ ካቡጋ አዝኒዬር ሱር ሴን በተሰኘ ሥፍራ ማንታቸውን ቀይረው እየኖሩ እንደነበርም አስታውቋል።
ዓለም ዐቀፉ የሩዋንዳ ወንጀል ችሎት የ84 ዓመቱን ግለሰብ በዘር ማጥፋት ወንጀል እና የሰው ልጅ ላይ ሰቆቃን በመፈፀም ወንጀል ለዘመናት ሲያፈላልጋቸው ነበር::
በፈረንጆቹ 1994 የሁቱ አክራሪዎች 800 ሺህ ያክል ሰዎችን ሲጨፍጭፉ፣ ሰውዬው አክራሪዎቹን በገንዘብ ደግፈዋል በሚል ይጠረጠራሉ። አሜሪካ ካቡጋ ያለበትን ለጠቆመ 5 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት እሰጣለሁ ብትልም ግለሰቡ ሳይያዙ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል።
በሄግ የሩዋንዳን ጉዳይ የሚከታተሉት ዋና ዐቃቤ ሕግ እንደገለፁት ከሆነ ፈረንሳይ ሰውዬውን ልታገኝ የቻለችው ከብዙ ፍለጋና ድብቅ ኦፕሬሽን በኋላ መሆኑን አመላክተው፤ የፌሊሲዬን ካቡጋ መታሠር የዘር ማጥፋት ወንጀል በመፈፀም የተጠረጠሩ ሰዎች ከ26 ዓመታት በኋላ ሊያዙ እንደሚችሉ ማሳያ ነው ብለዋል።
በፈረንሳይ ሕግ መሠረት አስፈላጊው ምርመራ ከተደረገላቸው በኋላ ወደ ዓለም ዐቀፉ የሩዋንዳ ዘር ማጥፋት ወንጀልን ወደሚመለከተው ችሎት ተላልፈው፣በዚያ ፍርዳቸውን መከታተል እንደሚችል ተገልጿል።
ዘር ማጥፋትና የዘር ጥፋት ማነሳሳት በመሳሰሉ ሠባት ወንጀሎች ከ1997 (እ.ኤ.አ) የሚፈለጉት ካቡጋ፤ ካቡጋ የፎ ደ ዴፎንስ ናሲዮናል ወይም ኤፍ.ዲ.ኤን
የተሰኘው ድርጅት ተባባሪ መሥራች ነበሩ:: ይህ ድርጅት ለወቅቱ የሩዋንዳ ጊዜያዊ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ የዘር ማጥፋቱ እንዲፋፋም አግዟል በሚል በአሜሪካ የተከሰሰ ተቋም ነው።
ካቡጋ ከገንዘብ ድጋፍ ባሻገር፤ ለታጣቂዎች የሎጂስቲክ መረጃ በመስጠት ፣ እንዲሁም የወታደር መለያና መሣሪያ በማስታጠቅ የዘር ጥፋቱን አፋፍመዋ በሚል በጥብቅ ሲፈለጉ ቆይተው ከ25 ዓመት በኋላ ተይዘዋል::