ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በደቡብ ክልል፤ ጉራጌ ዞን ባሉት “መስቃን” እና “ማረቆ” በተሰኙት ወረዳዎች መካከል ተፈጠረ በተባለ ግጭት የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የዞኑ አስተዳደር ገለፀ።
በኹለቱ ወረዳዎች በተለያዩ ጊዜያት የሚነሱት ግጭቶች ለሰዎች ሕይወት ማለፍ ምክንያት መሆናቸው እንደቀጠለ እየተነገረ ነው።
በዚህ መልክ ሰሞኑን በዞኑ ኹለት ወረዳዎች መካከል በተነሳ የግለሰቦች ፀብ የሦስት ሰዎች ሕይወት ሊያልፍ መቻሉን ያረጋገጡት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ መመመድ ጀማል ፤ ይሁን እንጂ በአሁኑ ሰዐት በአካባቢው ያለው የፀጥታ ኃይል ግጭቱን በጊዜ ማስቆም መቻሉን ፣ በዚህ ወቅት ዞኑ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
የስርቆትና የእርስ በእርስ ትንኮሳዎች እንዲሁም የተለያዩ ምክንያቶች ለማረቆና መስቃን ወረዳዎች የግጭት መነሻ መሆናቸውን የተናገሩት መሐመድ፣ በወረዳዎቹ መካከል በተደጋጋሚ የሚፈጠረውን ግጭት ለማስቆም ጥረቶች ቢደረጉም ችግሩን በዘላቂነት መፍታት ያለመቻሉንም አስታውቀዋል።
ቀደም ሲል በወረዳዎቹ መካከል ሰላምን ለመፍጠር ተደጋጋሚ ወይይቶች የተደረጉ ሲሆን ለችግሩም ተጠያቂ ናቸው የተባሉ አካላት ለፍርድ እንዲቀርቡ ተደርጎ ነበር። ይሁን እንጂ ችግሩን የሚፈጥሩ ግለሰቦች የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ በሆደ ሰፊነት ለማለፍ አለመቻላቸው ግጭቱ ዛሬም ድረስ እንዲቀጥል ምክንያት መሆኑን ሓላፊው አስረድተዋል።