ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ኢትዮጵያ ውስጥ የኮሮና ቫይረስ መግባቱ ከተሰማ በኋላ ከፍተኛው ቁጥር የተመዘገበበት የኮቪድ 19 ቫይረስ ተጠቂዎች መገኘታቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ባለፉት 24 ሰዐታት ውስጥ በተደረገ የላብራቶሪ ምርመራ ከእስከ ዛሬው ከፍተኛ የሆነ የኮሮና ቫይረስ ታማሚ ተገኘ ያለው ሚኒስቴሩ፤ 1 775 (አንድ ሺኅ ሠባት መቶ ሠባ አምስት) የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጎ 35 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው ይፋ አድርጎል፡፡ ይህ ከፍተኛ አኃዝ በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙትን ሰዎች ቁጥር 352 (ሦስት መቶ ሀምሳ ሁለት) አድርሶታል፡፡
ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው 17 ወንድና 18 ሴት ናቸው ያለው የጤና ሚኒስቴር መግለጫ፤ ሁሉም በቫይረሱ የተያዙት ሰዎች ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ እድሜያቸው ከ15 እስከ 80 ይደርሳል ብሏል፡፡
ከ35ቱ የኮሮና ተጠቂዎች 29ኙ ከአዲስ አበባ፣ 1 ሰው ከኦሮሚያ ክልል፣ 4 ሰዎች ከሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ለይቶ ማቆያ የተገኙ ሲሆን፤ በተጨማሪ 1 ሰው ከአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬ ከተማ ለይቶ ማቆያ መገኘቱ ተገልጿል ።
ሀያ አራቱ ሰዎች በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት ያላቸው፣ ስድስቱቱ የውጪ ሀገር የጉዞ ታሪክ ያላቸው፣ ቀሪዎቹ አምስቱ ሰዎች ደግሞ የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት የሌላቸው መሆኑን የጠቆመው የጤና ሚኒስቴር መግለጫ፤ በትናንትናው ዕለት ሦስት ሰዎች ከበሽታው ማገገማቸውንና በአጠቃላይ ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 116 መድረሱን አስታውቋል፡፡