ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ከ800 ግራም በላይ ወርቅ በተሸከርካሪ ውስጥ ሆነው እየመዘኑ ሲከፋፈሉ የተገኙ ሦስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ፖሊስ ገለፀ።
ግለሰቦቹ ቀደም ሲል በአንድ የወርቅ መሸጫ ሱቅ ላይ የስርቆት ወንጀል መፈፀማቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ማግኘቱን የሳሪስ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ይፋ አድርጓል።
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ወረዳ 10 ፣ “ዳማ ሆቴል” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ባለ የወርቅ መሸጫ ሱቅ ገዢ መስለው በቀረቡ ሰዎች 60 ሺኅ ብር ግምት ያላቸው የጣት ቀለበቶችን መሰረቃቸውን ማሳወቃቸውን ተከትሎ፤ ፖሊስ የወንጀል ፈፃሚዎቹን ማንነት በማወቅ ለመያዝ ክትትል እያደረገ ባለበት ሁኔታ፣ ግንቦት 6 ቀን 2012 ዓ/ም በክፍለ ከተማው ወረዳ 9 ቶታል ተብሎ በሚጠራው ቦታ፤ ሦስቱ ግለሰቦች በተሽከርካሪ ውስጥ ባለ14፣ ባለ 18፣ እና ባለ 21፣ ካራት ወርቆችን ሲከፋፈሉ ተይዘዋል።
ተጠርጣሪዎቹ ሢያዙ፤ በአጠቃላይ 886 ግራም ወርቅ ይዘው እየመዘኑ ሲከፋፈ፣ በክትትል ፖሊስ አባላት በጥርጣሬ ውስጥ ሊወድቁ በመቻላቸው በሕግ ቁጥጥር ሥር ለመዋል በቅተዋል ብሏል ፖሊስ።
ከወርቁ በተጨማሪ ከአንደኛው ግለሰብ እጅ ላይ በወቅቱ 80 ሺኅ ብር እንደተገኘ የገለፁት ምክትል ኢንስፔክተር አበራ፤ በወቅቱ ሳሪስ ዳማ ሆቴል አካባቢ የስርቆት ወንጀል በተፈፀመበት የወርቅ መሸጫ ሱቅ ውስጥ የተገጠመው የደህንነት ካሜራ የፈፃሚዎቹን ማንነት ቀርፆ እንደነበረ እና በካሜራው ወንጀሉን ሲፈጽሙ የታየው ምስል ውስጥ ወርቁን ሲከፋፈሉ ከተያዙት የሦስቱ ግለሰቦች ምስል መገኘቱን አስረድተዋል።
በተጠርጣሪዎቹ ላይ ምርመራ እየተጣራ ነው ያሉት ሓላፊው፤ ገዢ መስለው የሚመጡ ሁሉ ገዢ ስላልሆኑ በተለይም የወርቅ ጌጣ ጌጦች በቀላሉ ሊያዙና ሊደበቁ የሚችሉ በመሆኑ በጌጣ ጌጥ መሸጫ ሱቆች ላይ የሚሠሩ ሠራተኞችና ነጋዴዎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።