ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ኢትዮጵያ ከወጪ ንግድ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 2.09 ቢሊዮን (ሁለት ነጥብ ዘጠኝ) የአሜሪካን ዶላር ገቢ ማግኘቷ ተነገረ።
በ2012 በጀት ዓመት 9 ወራት 2.68 (ሁለት ነጥብ ስልሳ ሰምንት) ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ፣ 2.09 (ሁለት ነጥብ ዘጠኝ) ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት መቻሉን የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
አፈፃፀሙ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸር የ10 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ያመላከተው መግለጫ፤ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በዓለም ደረጃ የንግድ ግንኙነት የተቀዛቀዘ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ እያመረተች ያለችው ለምግብነት የሚውሉ ምርቶች በመሆናቸው ገቢው ሊጨምር መቻሉን አረጋግጧል::
በንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኮሙዩኒኩሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ፤ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እና ጫት በዘጠኝ ወራት ከተያዘላቸው እቅድ በላይ አፈፃፀም ማስመዝገባቸውን ጠቁመው፤ የብዕርና አገዳ እህሎች፣ የተፈጥሮ ሙጫና ዕጣን፣ ቡና፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት የእቅዳቸውን ከ75 በመቶ በላይ፣ ታንታለም፣ የቅባት እህሎች፣ የጥራጥሬ ሰብሎች፣ ስጋ፣ ቅመማ ቅመም፣ ባህር ዛፍ እና ሻይ ቅጠል የእቅዳቸውን ከ50 እስከ 74 በመቶ ገቢ አስገኝተዋል ሲሉ ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል ወርቅ፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች እና የቁም እንሰሳት የእቅዳቸውን ከ50 በመቶ በታች ዝቅተኛ ገቢ ያስገኙ ምርቶች እንደሆኑም ሓላፊው አስረድተዋል፡፡