ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡- ኢትዮጵያዊያውን ሉአላዊነታቸውን እና ብሄራዊ ጥቅማቸውን የሚዳፈር ማንኛውም አይነት ጫና እና ጥቃት ሲፈፀምባቸው በአንድነት ሆነ የመጋፈጥ ታሪክ ያላቸው መሆኑን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለፁ።
የኢዜማ ፓርቲ ሊቀመንበር ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ በኢቢሲ እንግሊዘኛ ቋንቋ ፕሮግራም ላይ በነቀራቸው ቆይታ፤ ከዓለም ዐቀፉ የህግ ድንጋጌ ማዕቀፍ ውጪ፣ በኢትዮጵያ ላይ የአባይን ተፋሰሶች ሲጠቀሙ የነበሩ ሀገሮች እና አሜሪካ የሚመጣ ጫና በምንም መልኩ ውጤታማ አይሆንም፤ በኢትዮጵያውያን ተቀባይነት የለውም ብለዋል።
“ሀቁን ትተው እንዲህ ዓይነት ስህተት ለመሥራት የሚዳፈሩት፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ በደንብ የማያውቁ ይመስሉኛል፤ አንድ ነገር አስረግጬ የምነግራቸው ፤ኢትዮጵያዊያን ሉአላዊነታቸውን እና ብሔራዊ ጥቅማቸውን የሚዳፈር ማንኛውም ዓይነት ጫና እና ጥቃት ሲፈፀምባቸው፣ በአንድነት ሆነው የመጋፈጥ ታሪክ ነው ያላቸው” ያሉት አስተዋዮ ምሁርና ፖለቲከኛ፤ ኢትዮጵያዊያን ይህን መሰል ሉዓላዊነታቸውን የሚዳፈር ጫና ከመቀበል፣ መራብን ነው የሚመርጡት ሲሉ ተናግረዋል።
“እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ለግብፅ፣ ለሱዳን እና በአባይ ተፋሰስ ተጠቃሚ ሀገራት የምለግሰው ቀና ምክር፤ ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት የሚመለከታቸው ተቀራርበው እንዲወያዩ፣ የጋራ ፍትኃዊ የሆነ ተጠቃሚነትን ሊያረጋግጥ የሚችል አፍሪካዊ መፍትኄ እንዲፈልጉ ነው” ያሉት አንጋፋው ፖለቲከኛና የሀገር ዐቀፉ ኢዜማ ፓርቲ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ “ከጅምሩ የአሜሪካ በአደራዳሪነት በአባይ ጉዳይ መግባቷን አልደገፍኩትም። ከአሜሪካ የሚመጣው ጫና የድርድሩን ውጤት ወደ አላስፈላጊ አቅጣጫ ከመግፋት በቀር የሚያመጣው አዎንታዊ ፋይዳ አይታየኝም።” በማለት በዶናልድ ትራምፕ አደራዳሪነት የተጀመረውን ጥረት ተችተዋል::