ፖለቲካ የማይፈታውን ጉዳይ በፖለቲካ ለመፍታት መታገል ሀገርን ብቻ ሳይሆን ራስንም ይሰብራል!|| ዮናታን...

ፖለቲካ የማይፈታውን ጉዳይ በፖለቲካ ለመፍታት መታገል ሀገርን ብቻ ሳይሆን ራስንም ይሰብራል!|| ዮናታን ተስፋዬ

ወዳጄ ብርሃነመስቀል ሰኚ ሌላ ዓለም ላይ ነው። ነገሩ እሱ እያወራ ያለው መቼ ለት “የጃዊ ካምፕ” ብዬ ከገለፅኳቸው የተለየ አይደለም። ይሄ ሀይል ኢትዮጵያዊነትን በመጠራጠር (detachment) ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ አቋም ነው የሚያራምደው።

በሌላ አገላለፅ በአንድ ወቅት በኤርትራ በረሃ “ግንቦት 7” ከከማል ገልቹ ጋር ለመስራት ድርድር ሲያደርጉ፤ ኦቦ ከማል “ኢትዮጵያ ፈርሳ ነው መሰራት ያለባት” ያሉት የፖለቲካ አቋም አይነት ነገር ማለት ነው። ይህን አቋም በማእከላዊ ሳለሁ ከአንዳንድ የኦፌኮ አባላት ሳይቀር እሰማው እና እከራከርበት ነበር።

ይህ ሀገር አፍርሶ የመስራት ህልም ከህልምነት ካለፈ ኢትዮጵያን ከመበትን የሚዘል ውጤት ይኖረዋል ብዬ አላምንም! ለምን ቢሉ በዚህ የተጠራጣሪነት መንፈስ ውስጥ አንድ አደገኛ አመለካከት አለ “ባጣ ቆየኝ”! የገዛ ሀገርህን በ”ባጣ ይቆየኝ” አመለካከት አካታች ሀገረ መንግስት አድርገህ ልትገነባ አትችልም። “እኔ በምፈልገው መንገድ ከሆነ ጥሩ ካልሆነ ግን…” በሚል የፖለቲካ አቋም የሚፈርስ እንጂ የሚገነባ ተቋምም አይኖርም እንኳን ሀገር።

ታሪክን እና ፖለቲካን ከአንድ አንግል ብቻ የመረዳት እና የመተንተን አባዜ የገዛ አባቶችህ የገነቡትን ወደ ማፍረስ ይሄዳል። ትናንትን በዛሬ መነፅር እያዩ በህይወት ያሉበትን አሁን እና ዛሬን ትተው ከትናንት ጥላ ጋር መጋጨት ነገን ማበላሸት ነው። በተለይ ዛሬም ወቅት እየጠበቀ በበሬ የሚያርስ ገበሬ ይዘን እና በእርዳታ ስንዴ አስከፊ ህይወት እየኖርን ማባሪያ የሌለው የፖለቲካ ትኩሳት ውስጥ መንገላታት ትርፉ ኪሳራ ነው።

ቢያንስ ሀገረ መንግስቱ ፈርሶ ተለያይቶ መኖር ቢቻል አንድ ነገር ነበር፤ ግን የአስተዳደር ወሰን በሆኑ ክልሎች ሳይቀር በስንቱ መሬት ላይ የይገባኛል ጥያቄ እየተነሳ በየዓመቱ ስንት ሰው ህይወት እንደሚቀጠፍ፣ የስንቱ ህልም እንደሚጨልም፣ የስንቱ ኑሮ እንደሚቃወስ ቤቱ ይቁጠረው። እዚህ ላይ ሌላ ሀገር አፍርሶ የመገንባት ህልም የሚፈጥረው የፖለቲካ ሽኩቻ ፍፃሜው ጤናማ ስለማይሆን ሊያስከትለው የሚችለውን ጉዳት ማሰቡ በራሱ አሰቃቂ ነው።

ይልቅስ ከዚህ ቀደም ራሱ ዶ/ር ብርሃነመስቀል ሲያቀነቅነው የነበረውን የቋንቋ ፖሊሲ ጉዳይ ቢገፋበት የተሻለ ይመስለኛል። ከዚህ በተጓዳኝ በአንድ ሀገር ውስጥ ያሉ ማንነቶችን ለማሳደግ ከፖለቲካ ይልቅ ኢኮኖሚ ያለውን ጉልህ ሚና መረዳት እና በዛ ላይ ኢንቨስት ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል። ይህን ትልቅ ፋይዳ ያለው ዘርፍ ትቶ ፖለቲካው ላይ ልሙትበት ማለት ለራስም ለሀገርም አይበጅም።

ማንነትን ለማሳደግ ከፖለቲካ ይልቅ የኢኮኖሚን ጉልበት መረዳት አስፈላጊ ነው – ለምሳሌ የኦሮሚኛ ቋንቋ እንዲያድግ አንዱ ቁልፉ ጉዳይ ስነፅሁፍ እና የመዝናኛ ኢንደስትሪ ነው። በዚህ ረገድ የኦሮምኛ ስነፅሁፍ ምን ያህል እየተደገፈ ነው? ፊልም የሚሰሩ፣ መፅሃፍ የሚፅፉ፣ መፅሄት ጋዜጣ የሚያሳትሙ፣ ወዘተ ስፖንሰር የሚያደርግ ሲቪክ ድርጅት ወይም ኢንቨስተር አለ? በዚህ ረገድ መጫና ቱለማ የሲቪክ ንቅናቄ በቀኃሥ ጊዜ እንኳን ለአፋን ኦሮሞ ያደረገውን አስተዋፅዖ 10% ያህል እያደረገ ያለ ማህበራዊ ንቅናቄ አለ?

ብዙ የብሔር ፖለቲካ አቅንቃኞች ችግሮችን ሁሉ በፖለቲካ ለመፍታት ሲንገላቱ፤ አማርኛም ይሁን ሌሎች ቋንቋዎች የተስፋፉበትን ከኢኮኖሚ ጋር የተያያዘ መሰረታዊ ጉዳይ ዘንግተውታል። ከተወሰኑት በስተቀር ብዙዎቹ የኦሮሞ ልሂቃን መፃህፍ ሲፅፉ እንኳን በአማርኛ ወይ በእንግሊዘኛ እንጂ በኦሮሚኛ ሲያሳትሙ አናይም – እንደውም በአፋን ኦሮሞ የታተመውን የዐብይን መፅሃፍ ሲያቃጥሉ የነበሩ ወጣቶችን ሲያበረታቱ ታዝበናል።

በጥቅሉ በፖለቲካ ሊፈታ የሚችለው የማንነት ጥያቄ ውስን መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። የፖለቲካ አቅም አለኝ ብለህ በህግ ብቻ ልትተገብረው የምትችል ነገርም አይደለም የማንነት ጉዳይ። ባህል፣ ቋንቋ፣ ወግ… ማህበራዊ እሴት የተባለ ነገር ሁሉ በማህበራዊ መስተጋብር፣ በገበያ ትስስር እና በፈቃድ ላይ የሚመሰረት እንጂ በፖለቲካ ውሳኔ እና አስገዳጅ ህግ ተፈፃሚ መሆን የሚችል አይደለም።

ማህበራዊ እሴቶችን በተመለከተ የፖለቲካ ውሳኔ ብታሳልፍ እንኳን የፖለቲካ ሰነድ ላይ በደማቅ ቀለም ከመስፈር የዘለለ ብዙም ማህበራዊ ለውጥ ሊያመጣ አይችልም። ሌላው ሌላው ሙግት ቢቀር እንኳን በዚህ በ21ኛው ክ/ዘመን ማርኬት ሁሉንም ነገር ዲክቴት በሚያደርግበት፤ የፖለቲካ ውሴኔ ብዙ ፋይዳ እንደሌለው – በመሰረታዊነት የማንነት ጥያቄዎችንም ሊፈታ እንደማይችል አዙሮ ማየት የተሻለ መፍትሄ ለመሻት እድል ይፈጥራል።

ሰላማችን ይብዛ!

LEAVE A REPLY