ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከእንግሊዝ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ጄምስ ፊሊፕ ደድሪጅ ጋር በቪዲዮ ኮንፈረንስ ውይይት ማድረጋቸው ተነገረ፡፡
ሚኒስትሮቹ በውይይታቸው የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን በትብብር መግታት በሚቻልባቸው ጉዳዮች፣ በቀጠናዊ ጉዳዮች እና በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ መክረዋል ነው የተባለው።
አቶ ገዱ እንግሊዝ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ከኢትዮጵያ ጋር እያደረገች ላለው ትብብር እና ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው ፤ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በዓለም ላይ እና በተለይም በእንግሊዝ በደረሰው የበርካታ ሰዎች ሞት ሀዘናቸውን መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በድህረ ገፁ አስነብቧል።
ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን እስከዛሬ ድረስ ያደረጉትን ውይይት በተመለከተም በቂ ገለጻ ያደረጉት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ፤ ኢትዮጵያ የግድቡን ዉሃ የመጀመሪያ ሙሌትበቅርቡ እንደምታካሂድ እና በግብጽ በኩል የተያዘው የተሳሳተ አመለካከት በሦስቱ አገሮች በሚደረግ ውይይት እና ንግግር ሊፈታ የሚችል መሆኑን በመጠቆም ፣ ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ግብጽ ወደ አቋረጠችው ሦስትዮሽ ውይይት እንድትመለስ ጥረት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
የእንግሊዝ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ጄምስ ፊሊፕ ደድሪጅ ኢትየጵያ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ለምታደርገው እንቅስቀሴ እንግሊዝ ትብብሯንና ድጋፏን አጠናከራ እንደምትቀጥል ገልጸው፤ የጤና ሚኒስቴር፣ የአፍሪካ በሽታዎች መቆጣጠሪያ ማዕከል እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ደረጃ የኮሮና በሽታ ስርጭትን ለመከላከል እያደረጉ ያለውን ጥረት አድንቀው፤ ኢትዮጵያ በቀጠናው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እያደረገች ያለውን እንቅሰቃሴም የሚበረታታ ነው ብለዋል።
ከኢትዮጰያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንበታ የውሃ ሙሊት ጋር በተያያዘ ሦስቱ አገሮች ልዩነታቸውን በውይይትና በድርድር እንዲፈቱ እንግሊዝ ድጋፏን እንደምታደረግም ሚኒስትር ጄምስ ፊሊፕ ደድሪጅ ቃል ገብተዋል፡፡