ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በኮቪድ-19 ሳቢያ ሰዎች ሲሞቱ ወይንም ህልፈተ ሐይወት ሲከሰት፤ አስከሬኑን በአግባቡ መሸኘትና ለቀብር ማዘጋጀት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ለባለሙያዎች ስልጠና ተሰጠ፡፡
በአስከሬን አያያዝና አቀባበር ዙሪያ ስልጠና የወሰዱ የጤና ባለሙያዎች፤ ለሥራው ለተመረጡ የፖሊስ አባላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በቀጣይ እንደሚሰጡም የጠቆሙት የፌደራል ፖሊስ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር እስክንድር ሳህሉ፤ ኮቪድ 19 ተላላፊ በመሆኑ የተለየ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ አስታውሰዋል።
በበሽታው ምክንያት ሕይወታቸውን በሚያጡ ሰዎች የቀብር ሥነ ሥርአት ላይ የሚሳተፉ የፖሊስ አባላት፣ ከራስ እስከ እግር ድረስ የበሽታው መከላከያ መሳሪያዎችን መጠቀም እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
በተጨማሪም ርቀታችን መጠበቅ፣ እጃችንን በውሃና በሳሙና መታጠብ፣ ሳኒታይዘር፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ መጠቀም እንዲሁም ከአቅም በላይ ካልሆነ በስተቀር ከቤት አለመውጣት ቫይረሱን ለመከላከል ቁልፍ ምክሮች በመሆናቸዉ ዘወትር ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል እነዚህን መመሪያዎች ሊተገብር ይገባል ብለዋል፡፡