ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ መሐመድን ከስልጣን እንዲነሱ በጠየቁ አባላት በተነሳ ውዝግብ ምክር ቤቱ የ12 አባላትን ያለመከሰስ መብት አነሳ።
ስብሰባ ሳያካሂድ ወራትን ያስቆጠረው የክልሉ ምክር ቤት ሐሙስ ዕለት በጠራው ስብሰባ ላይ ከያዛቸው አጀንዳዎች ባሻገር በምክትል ፕሬዝዳንቱ አስተዳደር ላይ በመወያየት የመተማመኛ ድምጽ እንዲሰጥ በጠየቁ አባላት አማካይነት ውዝግብ ተከስቷል።
ከሁለቱም ወገኖች በኩል በአጀንዳው ላይ ያለቸውን ልዩነት ስላሰሙት የምክር ቤቱ አባላት ብዛትን በተመለከተ የተለያዩ ቁጥሮች ቢሰጥም በጉባዔው ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ የተወሰነባቸው አባላት ቁጥር 12 መሆኑን አንድ የክልሉ ምክር ቤት አባል ለቢቢሲ ገልጸዋል።
“እርምጃው ሕገ ወጥ ነው” ያሉትና ያለመከሰስ መብታቸው ከተነሳው የምክር ቤቱ አባላት መካከል አንዱ የሆኑት አቶ አብዱራህማን ኦራቴ፤ በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ለመታደም 180 አባላት መገኘታቸውንና በምክትል አፈጉባኤዋ አማካይነት ለዕለቱ የተያዙት የስብሰባ አጀንዳዎችን ወደ ማጽደቅ ሲገባ አለመግባባትና ረብሻ መከሰቱን ገልጸዋል።
ይህን ተከትሎ የተወሰኑ የምክር ቤቱ አባላት ከአጀንዳው ውስጥ የክልሉ መንግሥት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ይጨመርበት የሚል ሐሳብ ቢያቀርቡም፤ ይህ አጀንዳ ተቀባይነት ባለማግኘቱ የተወሰኑ አባላት ስብሰባውን ጥለው ወጥተዋል ይላሉ አቶ አብዱራህማን።
“ከአዳራሹ ውጪ ለጋዜጠኞች ስለክስተቱ መግለጫ መስጠት ስንጀምር በፖሊስ ጥቃት ደርሶብናል። የተወሰኑ የምክር ቤቱ አባላት ላይ ድብደባ ተፈጽሟል” ያሉት አቶ አብዱራህማን ኦራቴ እርሳቸውን ጨምሮ በሌሎች የምክር ቤቱ አባላት ላይ ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳበት ሂደት አግባብ አይደለም ሲሉ የሙስጠፌ መሐመድን አመራር በእጅጉ ኮንነዋል ።