ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– አሰቸኳይ ስብሰባውን ያካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ባደረገው ውይይት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
ካቢኔው ባደረገው መደበኛ ስብሰባ በታክስ እዳ ማቅለያ እና ገቢ መሻሻያ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ሲያሳልፍ፤ ከ1997- 2007 ዓ ም ግብር ዘመን ውዝፍ እዳ ለነበረባቸው ግብር ከፋዮች እዳው በምህረት ቀሪ እንዲደረግላቸው ከሰምምነት ላይ ደርሷል።
የታከለ ኡማ ካቢኔ ከ2008 – 2011 ግብር ዘመን እዳ ላለባቸው ግብር ከፋዮች ደግሞ። ቅጣትና ወለድ ተነሥቶ ፍሬ ግብር ብቻ እንዲከፍሉ ውሳኔ አሳልፏል።
በሌላ በኩል የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር ሲባል ቤታቸው ለተቀመጡ ሠራተኞች ደሞዝ ለሚከፍሉ ድርጅቶችና ግለሰቦች፤ እንዲሁም ለተከራዮቻቸው የኪራይ ቅናሽ ላደረጉ አከራዮች፤ የታክስ ጫና ማቃለያ ይረዳሉ ያላቸውን ውሳኔዎች ማሳለፉን አስታውቋል፡፡
የታክስ መሰረትን በማስፋት፣ ማዘጋጃ ቤታዊ እና የከተማ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን አቅምና አሠራር በተሻለ መልክ በማደራጀት የ2013 ዓም በጀትን በመካከለኛ ገቢ ምጣኔ መሠረት ተዘጋጅቶ ለውይይት እንዲቀርብም ጉባዔው ወስኗል።