ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 24 ሰዐታት ውስጥ በተደረገ የ4 ሺኅ 48 የላብራቶሪ ምርመራ 88 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው ተነገረ።
ይህን ተከትሎ በኢትዮጵያ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 582 መድረሱን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ዛሬ ይፋ አድርገዋል።
በሀያ አራት ሰዐቱ ምርመራ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፤ እድሜያቸው ከ8 እስከ 75 ዓመት የሆኑ 51 ወንዶችና 37 ሴት መሆናቸው ታውቋል።
ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል 55 ሰዎች ምንም ዓይነት የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ እና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት የሌላቸው፣ 13 ሰዎች የውጭ የጉዞ ታሪክ ያላቸው እንዲሁም 20 ሰዎች በበሽታው ከተያዘ ሰዎች ጋር ግንኙነት ያላቸው መሆኑን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
በዚህም ቫይረሱ በምርመራ ከተገኘባቸው ሰዎች ውስጥ 73 ሰዎች ከአዲስ አበባ ሆነዋል። በዚህም መካከል 50 ሰዎች የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ እና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት የሌላቸው፣ 19 ሰዎች በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት ያላቸው እንዲሁም 1 ሰው ደግሞ የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ ያላቸው በመሆን ተመዝግበዋል።
8 ሰዎች ከትግራይ ክልል (ሁሉም የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ ያላቸው)፣ 4 ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል (2 ሰዎች የውጭ የጉዞ ታሪክ ያላቸው እና 2 ሰዎች ደግሞ የጉዞ ታሪክ እና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት የሌላቸው፤ ነዋሪነታቸው አምቦ፣ ቡራዩ፣ ሰንዳፋ እና ሞጀኖ ከተሞች)፣ 1 ሰው በሀረሪ ክልል ክልል (በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት ያላት) እንዲሁም 2 ሰዎች የውጭ የጉዞ ታሪክ ያላቸውና የድንበር ተሻጋሪ መኪና አሽከርካሪዎች መሆናቸውንም የጤና ሚኒስትር አስታውቋል።
በተደረገው የላብራቶሪ ሜርመራ ከተለያዮ ይበልጥ ተጋላጭ ከሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ ከጤና ተቋማት፣ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ ካላቸው ሰዎች እንዲሁም በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ካሉ ሰዎች የተወሰደ መሆኑም ታውቋል።