የሕገ-መንግስት አጣሪ ጉባኤ || ፍሬሕይዎት ሳሙኤል

የሕገ-መንግስት አጣሪ ጉባኤ || ፍሬሕይዎት ሳሙኤል

የሕገ-መንግስት አጣሪ ጉባኤ የተቀበለዉን የሕግ ባለሙያዎቸን ማብራሪያና የምርጫ ቦርድን ገለፃን በትኩረት ተከታትዬአለሁ። ፖለቲካውን ለፖለቲከኞች ትተን፤ የጉዳዩን ፈይዳ ሀላፊነት በሚሰማን መልኩ ካየነው —

ይህ አይነት ጅምር በራሱ መበረታተት ያለበት መሆኑን መግለፅ አስፈላጊ ነው። ኢትዮጵያ ለበርካታ አመታት ህግና ህገ-መንግስት ወደ ጎን ተትቶ በፖለቲከኞች ሁሉም ውሳኔዎች ሲሰጥበት የነበረ ሃገር ነው፨ አሁን የህግ እና የህገ-መንግስት ጉዳይ ከፖለቲካ ሜዳ ወጥቶ በህግ ባለሙያዎች ውይይት መደረጉ በራሱ ትልቅ እርምጃ ነው። ከእንደዚህ አይነት አካሄድ ውሎ አድሮ ሁላችን ቢንጠቀም እንጂ አንከስርም። ግለሰቦች የበላይ ከሆኑበትና ከሚሆኑበት መንግስታዊ ስርዓት መላቀቂያው ብቸኛ መንገድ “የህግ የበላይነትን ማስፈን” ነው። በእኔ እምነት የሕገ-መንግስት አጣሪ ጉባኤ አካሄድ (ውሳኔያቸው ምንም ሆነ ምን ) የምንመኘውን የህግ የበላይነት ለማስፈን አንድ የመሰረት ድንጋይ ሊቆጠር የሚችል ተግባር ስለሆነ ሊበረታታ ይገባል።

የ1997 ዓ.ም የድህረ ምርጫ ሁከት አጣሪ ኮሚሽን ሰብሳቢ በነበርኩበት ወቅት “. . . የተመጣጠነ እርምጃ . . .“ ማለት ምን ማለት ነው? ምን ሲሆን ነው “. . . ያልተመጣጠነ/የተመጣጠነ. . .” የሚባለው . . ወዘተ በሚሉና ተዛማጅ ጥያቄዎች ላይ ከአሜሪካና ከአውሮፓ ባለሙያዎቸን ጋብዘን ማብራሪያ (ስልጠና) ሰጥተው ነበር። ማብራሪያ ከሰጡን ስዎች አንዱ ጄኔራል ዴቪድ ሮቤርትስ የሚባሉ የእንግሊዝ ጡረተኛ የጦር ጄኔራል ነበሩ ። እንዳሁኑ የአገር ውስጥ ባለሙያ ለመጠቀም ተችሎ ቢሆን ኖሮ አንድ እርምጃ ወደፊት መሄድ በተቻለ ነበር። በወቅቱ የእኛ የጦር ጄኔራሎች ወይም ሌሎች ባለሙያዎች በጉዳዩ መብራሪያ መስጠት ስለማይቸሉ ሳይሆን ነፃነት ስላልነበራቸው ነበር መጠቀም ያልተቻለው። አሁን ግን በዚህ መልክ የሕገ-መንግስት አጣሪ ጉባኤ የጀመረው ሙያዊ ማብራሪያ የመጠየቅ አካሄድ ነገ በሌላም ጉዳይ ይጠቅመናል (አርቀን ካየን ፤ እና ከውይይቱ ማን ሊጠቀም ነው? በሚል ቁንፅል ጥያቄ ካልታሰርን ማለቴ ነው )።

ረጅም መንገድ በአንድ እርምጃ እንደሚጀመር ሁሉ ሙያዊን ጉዳይ በሙያው ባለቤት ማብራሪያ እንዲሰጥበት በማድረግ የተጀመረው የሕገ-መንግስት አጣሪ ጉባኤ አካሄድ ትንሽ የሚመስል ግን ብዙ ርቀት ሊወስደን የሚችል መንገድ ነው ለማለት ነው።

LEAVE A REPLY